ሰዉ ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ጥራት ያለዉ የላቦራቶሪ አገልግሎት እና የጤና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ከየካቲት 30 – መጋቢት 1/2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በክልሉ ያሉ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የላቦራቶሪ የዉጭ ጥራት ቁጥጥር ማዕከላት፣ ከኮቪድ-19 ምርመራ ማዕከላት፣ የግል ጤና ድርጅቶች ማሀበራት ተወካዮች፣ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በተገኙበት በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ባለፉት 6 ወራት ብቻ ሳይሆን ባለፈዉ 1 ዓመት በጣም ብዙና በብዙ ችግሮች ዉስጥ ነዉ ያለፍነዉ ካሉ በኋላ ከነዚህም ዉስጥ አንዱ የህብረተሰቡ ጤና ችግር የሆነዉ ኮቪድ-19 መሆኑንና የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በጣም በሰፊዉና በተሳካ ሁኔታ ተሰርቷል ለዚህም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸዉን ያቀረቡ ሲሆን በነበረዉ የህግ ማስከበር ዘመቻም የጤናዉ ሴክተር ሚና እጅግ የላቀ ነበር ያሉት ዶክተር መልካሙ አሁንም በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ሁሉ በመግባት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተቋሙ ጀማሪ ቢሆንም እያደረገ ያለዉ አስተዋፅኦ ቀላል የማይባል በመሆኑ አብሮ በመስራት፣ በመመካከር፣ በሰዉ ሀይልና በግብዓት ተቋሙን ማጠናከር፣ ማደራጀትና ማስፋት ይገባል ሁላችንም በየደረጃችን ለኢንስቲትዩቱ ድጋፋችንን የምንቀጥልና የህዝባችንን ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን ብለዋል ዶክተር መልካሙ፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸዉ ተቋሙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅልጥፍናና በብቃት ለመስራት በሚያስችል መልኩ መደራጀቱን ለዚህም በሰዉ ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ፣ የክልሉን ላቦራቶሪዎች ብቃት ባላቸዉ ባለሙያዎችና ጥራት ያለዉ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፍና ስልጠና እየሰጠ መሆኑንና እንዲሁም የጤና ምርምር ልማትን በጤናዉ ዘርፍ እንዲመራ በክልሉ መንግስት ለኢንስቲትዩቱ ሃላፊነት ተሰጥቶታል ለዚህም ቀላል የማይባሉ ተግባራት ተከናዉነዋል በዚህም ሰዉ ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋች በሰዉ ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ በርብርብ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በኢንስቲትዩቱ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሰጋ መንግስቱ የቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም ባለፉት ወራት በርካታ ሰዉ ሰራሽና የተፈጥሮ የጤና ስጋቶች በክልሉ መከሰታቸዉን ከነዚህም መካከል መፈናቀል፣ ዉሻን የሚያሳብድ በሽታ፣ ወባ፣ ኮቪድ-19 እና ኩፍኝ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸዉንና በኮቪድ-19 ምክንያት የ139 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን አሁንም በማህበረሰቡ ዉስጥ መዘናጋት እየተስተዋለ መሆኑንና የኮቪድ ምርመራ አፈፃፀም ዝቅተኛ ቢሆንም የተጠቂዎች ቁጥር ግን አሁንም ከፍተኛ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ እስካሁን 460811 ተፈናቃዮች መኖራቸዉንና ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም አሁንም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ የወባ ወረርሽኝን በተመለከተ ባለፉት 6 ወራት ከባለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ17 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ የኮቪድ-19 ምርመራ ማዕከላትን መስፋፋታቸዉ፣ ተፈናቃዮች ላይ የተሻለ ስራ መሰራቱ፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማሳለጫ ማዕከላትን በዞኖች ማስፋፋት መቻሉ፣ እዉቅና ያገኙ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን /Maintaining Accredited laboratory services/ ማስቀጠል መቻሉ የመሳሰሉት በጥንካሬ የሚነሱ ሲሆን ለተፈናቃዮች የምግብ መጠለያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የፀረ- ትንኝ ኬሚካል፣ ዉሻን ለሚያሳብድ በሽታ ክትባት እጥረት፣ የላቦራቶሪ ግብዓት እጥረት የመሳሰሉት በ6 ወሩ ለኢንስቲትዩቱ ፈታኝ ሁኔታዎች ተብለዉ ተገምግመዋል፡፡ በክልሉ ጤና ቢሮ ተጠሪ ከሆኑ 5 ኮሌጆች ጋር የምርምር ስራዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ፣ ለላቦራቶሪ መሳሪያዎች ጥገና የባዮ ሜዲካል ወርክሾፕ አለመኖር፣ ዉሻን ለሚያሳብድ በሽታ ክትባት የግብዓት እጥረት መኖር፣ ኮቪድ-19ን በተመለከተ በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም ከክፍያ ጋር በተያያዘ በባለሙያዎች ቅሬታዎች መፈጠራቸዉ፣ ተፈናቃዮችን በተመለከተ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች ተፈናቃዮች ባሉባቸዉ ቦታዎች ለመስጠት የባለሙያ እጥረት መግጠሙን አስተያየት ሰጭዎች አንስተዋል፡፡ ከተሳታፊዎች በተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የስራ ክፍል ኃላፊዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በማጠቃለያዉ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ማህበረሰቡን ማገልገል የጋራ ግዴታችን በመሆኑ በትብብር አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም መስራትና ለዉጥ ማምጣት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *