በራንች/ቻግኒ የተፈናቃዎች ጣቢያ ሲሰቱ ለነበሩ የጤና ባለሙያዎች እና ጤና ተቋማት የእዉቅናና የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አዳጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለዉ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ ከህዳር እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም በራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለዉ ለነበሩ ከ 79041 በላይ ተፈናቃዮችን የጤና አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ 32 የጤና ባለሙያዎች እና 3 የጤና ተቋማት (የቻግኒ ሆስፒታል፣ ቻግኒ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እና ቻግኒ ጤና ጣቢያ) የእዉቅናና የምስጋና ፕሮግራም ሃምሌ 3/2013 ዓ.ም አካሄደ፡፡ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አምሳሉ በፕሮግራሙ ላይ ሰብዓዊነት የተሞላበት እና ከየትኛዉም የመደበኛ ስራዎች ጋር የማይነፃፀር አገልግሎት ሰጥታችኋል፤ ለህዝባችሁ ወገንተኝነትን አሳይታችኅል፤ ቤታችሁንም ትታችሁ ለተፈናቃዮች አገልግሎት ስለሰጣችሁ ላቅ ያለ ምስጋና ያስፈልጋችኋል ብለዋል፡፡ አቶ አብርሃም አያይዘዉም በርካታ ችግሮች ገጥመዉን የነበረ ቢሆንም በነበረዉ የተጠናከረ የትብብር ስራ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት ዞን የመመለስ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በራንች የመጠለያ ጣቢያም ደመወዝ የሌላቸዉ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ጭምር የጤና አገልግሎት ሲሰጡ ከርመዋል ብለዋል፡፡ በራንች /ቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ላይ ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማሳለጫ ማዕከል/Osite PHEOC/ አቋቁሞ የጤና ባለሙያዎችን፣ መኪና እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመመደብ ለ8 ወር ያክል ምላሽ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ይህ አይነቱ አሰራርም ለተፈናቃዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለን የአሰራር ዘዴ በመሆኑ በምርጥ ተሞክሮነት ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ከኢንስቲትዩቱ በኩል ተመድበዉ በራንች የተፈናቃዮች ጣቢያ ሲሰሩ በቆዩት ባለሙዎች (አቶ ተፈራ አለሙ እና በአቶ አበበ ሲሳይ) ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ለተፈናቃዮች ሲሰጥ የነበረዉ የጤና አገልግሎት በ4 ዋና ዋና አምዶች የተደራጀ ሲሆን እነሱም፡- የታመሙ ሰዎችን የማከም፣ የግልና የአካባቢን ንፅህና የመጠበቅ፣ የህብረተሰብ ጤና ቅኝት እና የጤና አጠባበቅ ትምህርት ናቸዉ ብለዋል ባለሙያዎች፡፡ ከዚህም ባለፈ የጤና ቡድኑ የምግብ ስርጭቶችን እና የተፈናቃዮችን መረጃ የማጥራት ስራዉን ሲደግፍና ሲያግዝ ነበር ብለዋል አቶ ተፈራ፡፡ እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ እንደዚህ ዓይነት የህብረተሰብ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሁሉንም ሴክተር መስሪያ ቤቶችን እና ሁሉንም የመንግስት የአስተዳደር እርከኖችን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማሳለጫ ማዕከል/EOC/ECC/ ማቋቋም አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *