በተደራጀ መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለዉን ህመም፣ ሞት እና አጠቃላይ ቀዉስ መቀነስ እንደሚገባ ተገለፀ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ክልላዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ፣ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 አተገባበርና የቀጣይ 3 ወራት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ሚያዚያ 18/2013 ዓ.ም በደብረታቦር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነና ተከስቶ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በመሰራቱ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ በመሆን እዉቅና መገኘቱን አዉስተዉ አሁን ላይ የምርመራ መጠኑ ቀንሶ የኮሮና ቫይረስ የሚገኝባቸዉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ ነዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቫይረሱ ተይዘዉ ወደ ፅኑ ህሙማን የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተና የሞት ምጣኔዉም እየጨመረ ነዉ ብለዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የመከላከል ስራዎችን በተደራጀ መንገድ ለማስጀመርና የኮቪድ-19 መከላከል ስራን ከመደበኛ ተግባራት ጎን ለጎን ለማስኬድ መመሪያ ወደ ዞንና ወረዳዎች የማዉረድ ስራ መሰራቱንና ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወረርሽኙን ለመከላከልና የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ቅኝት ባለሙያ አቶ ተስፋሁን ታደገ የክልሉን የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታ መወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 17/2013 ዓ.ም ከ 263ሽህ በላይ የላቦራቶሪ ምርመራ እንደተደረገና 10ሽህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተጠቁ፣ 218 ሞት መከሰቱንና የሞት ምጣኔዉም 2.18 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ካሉ 11 የምርመራ ማዕከላት 6ቱ ብቻ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸዉን፣ ክትባት መዉሰድ ካለባቸዉ 77ሽህ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተቋም ሰራተኞች መካከል 32ሽህ የሚጠጉት ብቻ ክትባቱን እንደወሰዱ አቶ ተስፋሁን አክለዉ ገልፀዋል፡፡ እንደ ክልል ለጤና ባለሙያዎችና እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰጠዉ የክትባት መጠን 442ሽህ ዶዝ ቢሆንም መጠቀም የተቻለዉ 53ሽህ 539 ዶዝ (12%) ብቻ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘበናይ ቢተዉ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የተለያዩ ስራዎች መሠራታቸውን ገልፀዉ የኦክስጅን እጥረት፣ ለኮቪድ-19 ፅኑ ህሙማን የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት እንዳጋጠማቸዉ ገልፀዉ የበሽታዉ ስርጭት በመጨመሩ ከሚመረመሩት ውስጥ ከግማሽ በላይ ቫይረሱ እየተገኘባቸዉ መሆኑን፣ የሞት መጠኑም እየጨመረ መሆኑንና ወረርሽኙ ከቁጥጥር ዉጭ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ኮቪድ-19 ላይ ከክልል እስከ ወረዳ መዋቅር ተዘርግቶ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቢቆዩም አሁን ላይ መዋቅሮቹ ላይ መቀዛቀዝ መኖሩ፣ የኮቪድ መከላከያ ዘዴዎች መመሪያ አተገባበር ተፈፃሚ አለመሆኑ፣ የተፈናቃይ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ፣ የመጠለያ ቤት፣ ምግብ ነክ ግብዓቶች እጥረት፣ የኮቪድ መስፋፋት፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የትርፍ ጊዜ ክፍያ፣ የመሳሰሉት እንደ ችግር ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዋለ በላይነህ በዉይይቱ ላይ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎች አፈፃፀም መመሪያን መተግበር የብዙዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ርብርብ እንደሚያስፈልግና የፀጥታ መዋቅሩ የራሱን ድርሻ እንደሚወስድም ተናግረዋል:: በመጨረሻም ኮቪድን በመከላከል ተግባር ሌሎች ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ሁሉም የጤና ባለሙያ አርአያ በመሆን፣ ኮቪድ -19 ክትባቱ መውሠድና ሌሎችም እንዲከተቡ በማድረግ በአጭር ጊዜ አፈፃፀሙን ማሳደግ፣ እንደ ክልል የተጀመረው የኮቪድ መከላከል የቅንጅት ስራ እስከ ታች ጤና ተቋማትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከመደበኛ ስራዎች ጎን ለጎን መከላከሉን ውጤታማ ለማድረግ በተደራጀ መንገድ መስራት ይገባል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ በመድረኩ ከጤና ቢሮ፣ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ የዞን ጤና መምሪያ ሃላፊዎች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆችና ሜዲካል ዳይሬከተሮች፣ በክልሉ የኮቪድ አስተባባሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ አሕጤኢ ሚያዚያ 19/2013 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *