በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታን ለመከላከል ክትባት እንደሚሰጥ ተገለፀ፤

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከህዳር 18 እስከ 21/2013 ዓ.ም በክልሉ የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ ለመከላከል በዘመቻ ክትባት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ አንድ ተጠቂ ላይ የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ ኦሮሞ ብሔረሰብ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ ዞኖችን እና ደሴ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያው ዙር ክትባት ይሰጣል ብለዋል፡፡ በዘመቻው 6 መቶ 65 ሽህ 2 መቶ 84 ህፃናት የክትባት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ክትባቱ የሚሰጠው ቤት ለቤት በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ህጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ህፃን ክትባት ማግኘት እንዳለበት የገለፁት የቢሮው ሃላፊው የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ የቅኝትና የዳሰሳ ስራዎች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በክትባቱ ወቅት የሚሳተፋ ባለሙያዎች እና ወላጆች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ እጅን በውሃና በሳሙና በመታጠብ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ሃላፊው አሳስበዋል። የአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና አሰሳ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አሌ አያል በበኩላቸው ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በመስጠት፣ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራቱን ገልጸው ዘመቻውን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ አካላትን ያካተተ አደረጃጀት መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ ክትባት ከ15 ቀናት በኋላ ይካሄደል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *