በአማራ ክልል የኮቪድ-19 መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች አፈፃፀም በተመለከተ የተደረገው የጥናት ዉጤት ይፋ ሆነ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ ጤና ቢሮና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ያለውን እውቀት፣ ግንዛቤና ትግበራ (KPP) ላይ ትኩረት በማድረግ የተሰራ የዳሰሳ ጥናት ዉጤት በክልሉ ለተቋቋመ የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል አባላትና ለዉሳኔ ሰጭ አካላት ይፋ ተደረገ፡፡ የጥናቱ ዋና አላማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ ከተከሰተ በኋላ ወረርሽኙን መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች መካከል ዋና ዋናዎቹ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ ንጽህናን መጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ሲሆኑ በማህበረሰቡ ዉስጥ በተገቢዉ መንገድ ለምን እየተተገበሩ እንዳልሆነ እና ከቀን ቀን የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መሆኑ እየታወቀ ማህበረሰቡ ራሱን ለመጠበቅ መተግበር አለመቻሉ ምክንያቶቹ ምን እንደሆኑና እነዚህ የመከላከያ መንገዶች አተገባበር በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች ምን እንደሚመስሉ ለማወቅና የፖሊሲ አማራጮችን ለመስጠት ነዉ ተብሏል፡፡ ጥናቱ በክልሉ በሚገኙ ተጋላጭ 16 ከተሞችን የሸፈነ ሲሆን የመንግስት ተቋማት፣ ቤተ- አምልኮዎችን፣ ትራንስፖርት ላይ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ባንክ፣ ገበያ ቦታ፣ ጁስ ቤት ወዘተ.) እንደተካሄደ በውይይቱ ተገልጿል፡፡ በጥናቱ ግኝትም በማህበረሰቡ ዉስጥ የታየዉ 3ቱ የ”መ” ህጎች አተገባበር 12.7% መሆኑንና ይህ አተገባበር በተለያዩ አካባቢዎች ከ5% – 41% እንደሆነ እንዲሁም አብዛኛዉ የማህበረሰብ ክፍል ከወረርሽኙ መስፋፋት አንጻር የመከላከያ መንገዶችን እየተገበረ እንዳልሆነ በጥናት ቡድኑ ተመላክቷል፡፡ ለዚህ ትግበራ አፈፃጸም ዝቅተኛ መሆን በማህበረሰቡ ከተነሱት ዋና ዋና ምክንያቶች ዉስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ችግር ይፈጥራል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩ፡ የዉሃ አቅርቦት እና የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ችግር መኖሩ፣ የማህበረሰብ አኗኗር ዘይቤ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነባቸዉ በጥናቱ ወቅት የተሰበሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ ተብሏል በጥናት ቡድኑ፡፡ በጥናቱ የጎንደር፣ ደብረ ታቦርና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉ ሲሆን በመጨረሻም በጥናቱ የተገኙትን ውጤቶች ለፖሊሲ አማራጭ እንዲጠቀሙበት በምክረ-ሃሳቦች ተቀምጠዋል፡፡ በመድረኩ ሃሳብ አስተያየቶች ተነስተዉ ዉይይት የተደረገ ሲሆን በማጠቃለያዉ ላይ በምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ጥናቱ ጥሩ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ያሳዬመሆኑን ገልፀው በተሰጠው አስተያየት መሰረት ተስተካክሎ ለአገልግሎት እንዲውል ካሉ በኋላ መጭዉ የበዓል ወቅት በመሆኑ ገበያ ቦታዎች እና ትራንስፖርት አካባቢ መጨናነቆች ስለሚኖርና ለወረርሽኙ ስርጭት አመች ስለሚሆን ማስክ አማራ ዘመቻን አስቀጥለን የተሻለ ስራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡ አህጤኢ 5/13/2012 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *