በአንድ አካባቢ የሚከሰት የሕብረተሰብ የጤና ችግር ለየትኛዉም ቦታ ስጋት በመሆኑ ተገለፀ፤

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሕብረተሰብ ጤና አዳጋዎች ማሳለጫ ማዕከል ምንነትና ተግባራት፣ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች እና ሁሉን አቀፍ የዝግጁነት ተግባራት ላይ ያተኮረ ስልጠና ከታህሳስ 30 እስከ ጥር 1/2013 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ ተሰጥቷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ አሁን ባለው ሁኔታ ወረርሽኝ ከአንዱ አህጉር ወደ ሌላው በፍጥነትና በቀላሉ የመሰራጨት እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች ከመከሰታቸዉ በፊትና በሚከሰቱበት ወቅት ከመደበኛዉ አሰራር ስርዓት ወጣ ባለ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የብዙዎችን ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበት ዓላማ፣ ከሕብረተሰብ ጤና አዳጋዎች ቁጥጥር አኳያ ያለው ሚና እና የሕብረተሰብ ጤና አዳጋዎች ማሳለጫ ማዕከል ዓላማና ተግባራት ላይ ያተኮረ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቅድሚያ ስጋቶችንና ተጋላጭነትን የመለየት ሁኔታዎችን መዳሰስና የቅኝት ስራ በማከናወን ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ከወረርሽኝና አጠቃላይ ከስጋቶች ራሱን እንዲከላከል ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ የአብክመ ጤና ቢሮ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተክለኃይማኖት ገ/ህይወት በሕብረተሰብ ጤና አዳጋዎች ምንነት፣ በኢትዮጵያ ያለዉን የህብረተሰብ ጤና አዳጋ ስጋቶች፣ በወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅትና ማስጠንቀቂያ፣ ምላሽ አሰጣጥና ክስተትን መቆጣጠሪያ ስልቶች በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በአንድ አካባቢ የሚከሰት የሕብረተሰብ የጤና ችግር በየትኛዉም ቦታ ስጋት በመሆኑ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ነባራዊ ሁኔታዎችን አዉቆና ተገንዝቦ ለመስራትና ለመተባበር ስልጠናዉ አስፈላጊ ነዉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎች ከስልጠናዉ ያገኙት ግንዛቤ ጥሩ መሆኑን ገልጸዉ ዓላማችን ህብረተሰቡን ማገልገል በመሆኑ ሁሉም ተባባሪ ሆኖ በመስራት የወረርሽኝ መከላከል ስራ የኛ ብለን በመደጋገፍ እንሰራለን ብለዋል፡፡ በስልጠናው ከአብክመ ጤና ቢሮ እና የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት፣ ኬዝ ቲም አስተባባሪዎች እና ለሚመለከታቸዉ ባለሙያዎች ተሰሳትፈዋል፡፡ አሕጤኢ 3/5/2013 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *