በእብድ ውሻ በሽታ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት በእንስሳት ንክሻ በተለይም በዉሻ አማካኝነት የሚተላለፈዉን የእብድ ውሻ በሽታ በተመለከተ ከነሃሴ 25 እስከ 26/2012 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በባህርዳር ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የስልጠናዉ ዓላማ ከፍተኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር እያስከተለ ያለዉን የእብድ ዉሻ በሽታ የጤና፣ የእንስሳት ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት በቅንጅት በመስራት ስለዉሻ አያያዝ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ከፍ እንዲል፣ ባለቤት የሌላቸዉን ተልከስካሽ ዉሾች በተገቢዉ መንገድ ለመቀነስ፣ ዉሾች ክትባት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸትና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር መሆኑን የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰጭና መልሶ ማቋቋም ቡድን መሪ አቶ ኃይሉ አያሌዉ ተናግረዋል፡፡

በክልላችን ያለዉ ዉሻን የሚያሳብድ በሽታ ስርጭቱ በአስከፊ ሁኔታ ላይ በመሆኑና ለሰዉ  የሚሰጠዉ የድህረ ተጋላጭነት ክትባትና የዉሻ ክትባት አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ እያስከተለ ያለዉን ተፅዕኖ ለመቀነስ ማህበረሰቡ ዉሾችን እንዲያስከትብ በሚጠየቅበት ጊዜ ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት፣ ዉሾችን አስሮ እንዲጠብቅና በተጨማሪም በማንኛዉም እንስሳት በተለይም በዉሻ የመነከስ አደጋ ካጋጠመዉ በአስቸኳይ በአቅራቢያዉ ወደሚገኝ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባ አቶ ኃይሉ አሳስበዋል፡፡

ስልጠናዉ ከ15ቱም ዞኖች ለተመረጡ ጤና መምሪያ የዞን የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪዎች፣ ከእንስሳት ሃብት ልማት መምሪያ፣ የእንስሳት በሽታዎች ቅኝት ቡድን መሪዎች እና ከአካባቢ ደንና የዱር እንስሳት ጥበቃ መምሪያ ቡድን መሪዎች ለተዉጣጡ 42 ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡

አህጤኢ

28/12/12 ዓ.ም

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *