በክልሉ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል ሁሉም ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፤

የክልሉን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት፣ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ዕቅድ ከተለያዩ የክልል ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች ከጥር 5 እስከ 9/2013 ዓ.ም በዳንግላ ከተማ የተዘጋጀ ሲሆን በክልሉ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል ሁሉም ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ፣ በዓለም ጤና ድርጅት የኮይካ /WHO-KOICA/ ፕሮጀክት የአይበገሬ የጤና ስርዓት /Health System Resilience/ ቴክኒካል ኃላፊ ዶ/ር አብይ ግርማይ እና የአብክመ ጤና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተክለሃማኖት ገ/ህይወት በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት እና ምላሽ አሰጣጥ ዕቅድ አሰራር ሂደት እና አዘገጃጀት፣ የስጋት፣ የአደጋ እና ሌሎች ጉዳዮች አስመልክቶ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ በክልሉ የሚመለከታቸው የክልል ቢሮ ባለሙያዎች በዕቅድ ዝግጅቱ ላይ መሳተፋቸው ጥሩ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ በዕቅድ አፈፃፀሙ ላይም በጋራ ተባብሮ በመስራት ለክልላችን ማህበረሰብ የድርሻችንን ማበርከት አለብን ብለዋል፡፡ ዶ/ር አብይ በበኩላቸው ከክልሉ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የፌደራል ባለሙያዎች በማሳተፍ የክልሉ ጤና ሴክተር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት፣ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ዕቅድ መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን ገልጸው በአገር ደረጃ ተሞክሮ መሆን የሚችል ስራ በመሆኑ ወደ ዞንና ወረዳ መውረድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቶ ተክለሃይማኖት እንዳሉት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ሲከሰት በጋራ ለመስራት ዕቅድን በጋራ ማዘጋጀት መሰረታዊ ተግባር ነው ካሉ በኃላ የተዘጋጀውን የመጀመሪያውን ረቂቅ /zero draft/ ላይ የቀረውን በማጠናቀቅ ቶሎ አፀድቆ ወደ ስራ መገባት እንዲሁም በዕቅድ ዝግጅቱ ወቅት የተፈጠረውን የግንኙነት ስርዓት በማጠናከር በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ መድረኩን የአብክመ ጤና ቢሮ፣ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የዓለም የጤና ድርጅት ኮይካ /WHO-KOICA/ ፕሮጀክት በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ከጤና ቢሮ፣ ከኢንስቲትዩቱ፣ ከአብክመ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ከአብክመ ውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ፣ ከአብክመ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኤጀንሲ የመጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ አህጤኢ 10/05/2013
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *