በክልላችን የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ ተጀመረ፤

የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር ከጥቅምት 10-27/2013 ዓ.ም የሚከበረውን የወባ ሳምንት አስመልክቶ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ “ወባን ማጥፋት ከኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ቃል በክልል ደረጃ የሚከበረውን የወባ ሳምንት የወባ በሽታ መከላከልያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ለህብረተሰቡ በማስረፅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ የዘመቻው ዓላማ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ ሃይሌ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ላይ እንደተናገሩት በክልላችን ያለው የወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ የመጣ መሆኑን ገልፀልው የወባ ሳምንት መከበሩ የክልላችን ማህበረሰብ በወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ላይ አስፈላጊውን የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣና እንዲተገብር ያደርጋል ብለዋል፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ እንዳሉት የወባ በሽታ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ ተላላፊ በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን እና ይህን ለመከላከልና ለመቆጣጣር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልፀው የወባ ሳምንት ሲከበር የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር፣ የመኝታ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የወባ ምርመራ ማድረግ ለማህረሰቡ ግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መሰራት እንዳበት አሳስበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ፕሮግራም ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወ/ሮ ማስተዋል ወርቁ እንደገለፁት በያዝነው በጀት ዓመት በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል በ44 ወረዳዎች 217 ሺህ 393 ኪሎ ግራም የፀረ- ወባ ኬሚካል ተሰራጭቶ 340 ሺህ 39 ቤቶች የተረጩ መሆኑንና ከ988 ሺህ 881 ሰዎችን መታደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ በቆላማ እና በኢንቨስትመንት ያለባቸው ቦታዎች ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያ በማቋቋም ባለሙያዎችን ማሰማራት፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ ማሰማራት፣ ለማህረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ መስራት፤ የወባ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ማጠናከር እና የመኝታ አጎበር ማሰራጨት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሲሆን የፀረ ወባ ኬሚካልና መሳሪያ እጥረት መኖር፣ የወባ መድሀኒት አቅርቦት መቆራረጥ፣ አጎበርን በወቅቱ አለመተካትና አጎበርን የሚሸጡ ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ካጋጠሙ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ወ/ሮ ማስተዋል አስረድተዋል፡፡ የአማራ ክልል መሬት 80 በመቶው ለወባ መራቢያ ምቹ ሲሆን 68 በመቶው ህዝብ ደግሞ ለወባ ተጋላጭ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራትም 127 ሺህ 593 ሰዎች ተይዘዋል ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በቀጣይ የወባ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች የወባ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን ማጠናከር፣ በአጎበር አጠቃቀም ላይ ክትትል በማድረግ እና የማህበረሰቡን ግንዛቤ በመጨመር ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተላልፏል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *