በደም ዉስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን (Viral load) እና በደማቸዉ ዉስጥ ቫይረሱ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ (EID) ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (አሕጤኢ) የህክምና ላቦራቶሪ ዳይሬክቶሬት በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ በ8 ወራት በደም ዉስጥ ያለዉን የኤች አይቪ ቫይረስ መጠን (Viral load) እና ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት (EiD) ምርመራ ላይ የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በክልሉ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት (ART) የሚከታተሉ ሰዎች በተለያየ ምክንያት በደማቸዉ ዉስጥ ያለዉ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን ምርመራ በተሟላ ሁኔታ እየተሰራላቸዉ አለመሆኑንና ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ መሰራት የሚገባዉ ቢሆንም በተፈለገዉ ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቅሰዉ በነዚህ ተግባራት ስኬታማ መሆን ካልተቻለ ሊያስከትል የሚችለዉ ችግር ከፍተኛ ነዉ ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ለዝቅተኛ ተግባራት አፈፃፀም ምክንያቶችን ለይቶ በፍጥነት እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ በመግባት ከፍተኛ ለዉጥ ማምጣት ይገባል ካሉ በኋላ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያም የዳበረ ንቃተ-ህሊና ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአማራ ክልል የሲዲሲ ፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ መሰረት አዲሱ በክልሉ ያለዉን የ8 ወር የኤች.አይ.ቪ መከላከልና መቆጣጠር ስራ በጤና ተቋማት ያለዉን አፈፃፀም ምን እንደሚመስል በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እየሰጡ መሆኑን፣ 340 የመንግስት 33 የግልና መንግስታዊ ያልሆኑ ጤና ተቋማት ART እየሰሩ መሆናቸዉን እንዲሁም 5 የደም ዉስጥ ያለዉን የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን የሚሰሩ ማዕከላት መኖራቸዉንና 2 ተጨማሪ ማዕከላት (ወልዲያና ደብረታቦር) ስራ ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ መሰረት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ጠቅሰዉ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ በ2021 በክልላችን 208 ሽህ ሰዎች የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ፣ 7ሽህ 499 አዲስ ተጠቂዎች እንዲሁም 3ሽህ 162 በቫይረሱ ምክንያት ዓመታዊ ሞት ሊከሰት እንደሚችልም ተገምቷል ብለዋል፡፡ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ፣ መመርመር ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ቫይረሱ ያለባቸዉ እንደተገኙና ከተገኘባቸዉ ዉስጥም ምን ያህሉ መድሃኒት እንዲወስዱ እንደተደረገ መከታተል እንደሚገባ የተናገሩት ወ/ሮ መሰረት በክልሉ ባለፈዉ 8 ወር 470 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዉ መድሃኒት ማስጀመር እንዳልተቻለ ገልፀዉ ቫይረሱ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ከዓመታዊ ግብ 63.3 በመቶ በመሆኑ ከፍተኛ ስራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በክልሉ ባለፈዉ 8 ወር በ5ቱ በደም ዉስጥ ያለዉን የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን ምርመራ መጠን እና ቫይረሱ በደማቸዉ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ አፈፃፀም፣ በናሙና አላላክ ችግር ምክንያት የሚወገዱ ናሙናዎችን በተመለከተ የኢንስቲትዩቱ የቫይሮሎጅ ላቦራቶሪ ፎካል አቶ ደመቀ እንዳላማዉ አቅርበዋል፡፡ ከተሳታፊዎችም ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተዉ ዉይይት የተደረገ ሲሆን ከተለያዩ ተቋማት የሚመጡ የናሙና መቀበያ ፎርማቶች አንድ ወጥ አለመሆን፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ፣ ፖስታ ቤት ላይ ጠንከር ያለ ስራ አለመሰራቱ፣ የናሙና ጥራት መጓደል፣ የኤች.አይ.ቪ መመርመሪያ ኪት እጥረት፣ የግብዓት እጥረት፣ የመሳሰሉት እንደ ክፍተት ተነስተዋል፡፡ በመድረኩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮ የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ጨምሮ ከተለያዩ ዞኖች የተዉጣጡ ኃላፊዎችና የኤች.አይ.ቪ ኦፊሰሮች፣ የላቦራቶሪ አስተባባሪዎች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!! አሕጤኢ 20/7/2013 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *