በፖሊዮ ዘመቻ የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተዉጣጡ ባለሙያዎች በፖሊዮ በሽታ ክትባት አሰጣጥ ላይ የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ ተሰጠ፡፡ ስልጠናዉ በቀጣይ በክልሉ በሚካሄደዉ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተግባራት ወቅት የማህበረሰቡን ተሳትፎና ግንዛቤ ለማሳደግ በርካታ የመገናኛ አዉታሮችን እንደ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የጤና ሰራተኞችን በመጠቀም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ ማህበረሰቡን በማስተማር ለማበረታታትና ለማነሳሳት እንዲሁም የባህሪ ለዉጥ እንዲያመጣ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ በማዉጣት ለመተግበር የሚያስችል ነዉ፡፡ የክትባቱን አስፈላጊ፣ የፖሊዮ ዘመቻዉ መቼ እና የት የት አካባቢዎች እንደሚከናወን ለማሳወቅ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊስፋፋ የሚችል ጥርጣሬን ወይም የተሳሳተ ግንዛቤን ለማስወገድ፣ ፖሊዮ በልጆች ላይ ሽባነትን ወይም ሞት ሊያስከትል የሚችል በሽታ መሆኑንና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ልጆች ከዚህ በፊት ክትባቱን ቢወስዱም ባይወስዱም መከተብ እንዳለባቸው መልዕክቶችን በመቅረፅ በድግግሞሽና ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ አዉታሮችን ተጠቅሞ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በዘመቻዉም ባለድርሻ አካላት ማለትም የሃይማኖት መሪዎች፣ የህብረተሰቡ አመራሮች (የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች ፣ የሰፈር ሃላፊዎች፣ የትምህርት ቤት ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞች – ሚዲያ (ቲቪ / ሬዲዮ)፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ በልጆች ጤና እና ትምህርት ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሴቶች እና የወጣት መሪዎችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ፖሊዮ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ፣ በዋናነት በልጆች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርና በብዛት እድሚያቸዉ ከ5 ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የሚከሰትና ከ200 ኢንፌክሽኖች ውስጥ በአንዱ ላይ የማይቀለበስ ሽባነትን የሚያስከትል መሆኑ በስልጠናዉ የተገለፀ ሲሆን በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን በነሃሴ ወር 2012 ዓ.ም ሪፖርት የተደረገ መሆኑንና በኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ ዞን እና በደሴ ከተማ ለሚገኙ በጠቅላላዉ ከ8 መቶ ሃምሳ ሽህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡ በመድረኩም የፖሊዮ ዘመቻዉ በሚካሄድበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ሳይዘነጉ መሆን እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *