ኢንስቲትዩቱ ክልል አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የባለሞያዎች የንቅናቄ መድረክ አካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክልል አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የባለሞያዎች የንቅናቄ መድረክ ከሰኔ 5 እስከ 6/2013 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ አካሄዷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለፁት ባለፉት 9 ወራት በክልሉ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም፣ ወደፊት የሚፈጠሩ ክስተቶችን በተጠናከረ መንገድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በሀገር ደረጃ ብሎም በክልላችን የተጀመረዉን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ንቅናቄ ዘመቻ ላይ በመወያየት የመድረኩ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባለሞያዎች በማይመች ሁኔታም ዉስጥ ሆነዉ ሞያዊ ሃላፊነታቸዉን ለመወጣት እያከናወኑት ያሉ ተግባሮችን ከመቸዉም ጊዜ በላይ በማስቀጠል ለዉጥ በሚያመጣ መልኩ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የተከናወኑ ተግባራት በኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የስጋት ተግባቦት ኬዝ ቲም አስተባባሪ በአቶ አሌ አያል እንዲሁም ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 የንቅናቄ ዕቅድ የሕብረተሰብ ጤና ቅኝት ኦፊሰር በአቶ ተስፋሁን ታደገ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የሚመለከታቸዉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አምሳሉ በበኩላቸው ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ እንዲሁም በድጋፋዊ ጉብኝት በሁሉም ወረዳዎች መድረስ ስለማይቻል በየደረጃው ያለው መዋቅር የመደገፍና የማብቃት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በማጠቃለያዉ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁት እንደ ክልል የሃገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን፤ በግጭት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸዉ ጤና ተቋማት እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ ዞኖች እና ወረዳዎች ተናበዉ በመስራት ሕብረተሰቡን ማገልገል ሙያዊ ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባ እና የኮቪድ መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ስልቶችን በእቅዱ መሰረት በዉጤታማነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ሌሎች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የአብክመ ጤና ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸዉ በጤና ተቋማት የሚነሳዉ የሰዉ ሃይል፣ የመዋቅርና የደረጃ ጥያቄዎች ቢሮዉ ለመፍታት በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የስራ ላይ ስልጠናዎች መጠናከር እንዳለባቸዉ ይሁን እንጂ ሁሉንም የክልሉ ባለሞያዎች ማሰልጠን አቅም የማይፈቅድ በመሆኑ ስልጠና ያገኙት እዉቀትና ልምድ በማሸጋገር ረገድ ያለዉ ክፍተት መስተካከል እንዳለበት አቶ አብዱልከሪም ጠቁመዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት ዶክተር የሻምበል አጉማስ “እስኪሆን የመፋለም ቀመር ወቤተ ሙከራ” በሚል ርዕስ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ መድረኩ በ2 ዙር የተካሄደ ሲሆን የኢንስቲትዩቱና የጤና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣ አጋር አካላት፣ የዞንና የወረዳ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያዎች ከ 500 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!! አሕጤኢ 6/10/2013 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *