ኢንስቲትዩቱ ድጋፉን አጠናክሮ እየቀጠለ ነዉ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች የኢትዮጵያዊነት መለያ ባህሪ የሆነዉን መተሳሰብ፣ መደጋገፍና አብሮ የመኖር እሴት በተግባር ለመግለፅ ተቋሙ ካለዉ ዉስን ሃብትና በጀት በመቀነስ እንዲሁም ከተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዝ በመቀነስ አማራ በመሆናቸዉ ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲያደርግ የነበረዉን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል ዛሬም በአላማጣና ኮረም ከተማ አስተዳደሮች ስር ለሚገኙ አገልግሎት ሰጭ የመንግስት ሆስፒታሎች ግምታቸዉ ከ250ሽህ ብር በላይ የሚያወጡ የፅህፈት መሳሪያ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ፣ ዲስክቶፕ ኮምፒዩተር፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ለአንቡላንስ አገልግሎት የሚዉል የነዳጅ ኩፖን እና የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን በማስረከብ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡ ትህነግ የአማራን ህዝብ ለማጥፋት ጦርነት ቢያዉጅም በከፈተዉ ጦርነት ራሱ ከስር መሰረት ተነቅሎ በአማራነት ጥያቄያቸዉ መልስ ላገኙ የኮረምና የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታሎች የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ቋሚ እና አላቂ እንዲሁም የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን ድጋፍ ለማድረግ መገኘታቸዉንና ቀጣይም ድጋፍና ክትትሉ እንደሚቀጥል የድጋፉ አስተባባሪ አቶ እያደር መለሰ በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል፡፡ በርክክቡ ላይ የኮረም ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ገብረ ሚካኤል ታፈረ ሆስፒታሉ ከነ ችግሮቹም ቢሆን ሙሉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በአሰራር ላይ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር፣ የባለሙያ እጥረት፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ ባለፉት 8 ወራት እየተከፈለ አለመሆኑ እንደ ችግር አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረገላቸዉ ድጋፍም ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ወሳኝ በሆነ ሠዓት ድጋፉ በመድረሱ ትልቅ መፍትሄ መሆኑንና የተደረገዉ ድጋፍ ለአገልግሎት አሰጣጡ መቀላጠፍ ወሳኝ ሚና ያለዉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መክተ አበበ በበኩላቸዉ አሁን ላይ ተጠሪነታቸዉን አዉቀዉ ችግራቸዉን አቅርበዉ አድማጭ ማግኘታቸዉንና ሪፖርት ለአማራ ክልል እየላኩ መሆኑንና በተደረገላቸዉ ድጋፍ የተሰማቸዉን ሃሳብ ገልፀዉ ሆስፒታሉ ተጨማሪ ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም ትብብር እንዲያደርጉላቸዉ በአላማጣ ህዝብ ስም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የላቦራቶሪ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ ነዉ ለማለት አያስደፍርም ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ የባለሙያ ጥቅማ ጥቅም ክፍያ መክፈል እንዳልተቻለና ጥያቄዉንም ለዞንና ለክልል ማቅረባቸዉን ይህም የመንግስት አሰራርን ተከትሎ ተፈፃሚ እንደሚሆን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዉ ባለን አቅም ሁሉ የህክምና አገልግሎቱ እንዳይቆራረጥ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ሌላኛዉ አስተያየታቸዉን የሰጡት የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ፈንታ ኢንስቲትዩቱ በአይነት፣ በመጠን እና በይዘት ባደረገላቸዉ ድጋፍ መደሰታቸዉን ገልፀዉ ለተቋሙ የስራ ስልጠት ከፍተኛ ግብዓት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ አማረ ገለፃ ተከስቶ በነበረዉ ጦርነት ወቅት ሆስፒታሉ ቀንና ሌሊት ህብረተሰቡን ያገለግል እንደነበረ ገልፀዉ ሆስፒታሉ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ዉስጥ ሆኖ የቆየ በመሆኑ የቴስት ኪት መቆራረጥ፣ የተበላሹ ማሽኖች ጥገና አለመደረግ ዩመሳሰሉት ችግሮች እንዳሉባቸዉና እንዲሟሉላቸዉ ጠይቀዋል፡፡ የድጋፉ አስተባባሪም የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የክልሉ ጤና ቢሮ ሆስፒታሎቹ ላነሱት ጥያቄ በሚቻለዉ ሁሉ ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!!
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *