ኢንስቲትዩቱ 2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ነሐሴ 1/2013 ዓ.ም አካሄደ፡፡ በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የኢንስቲትዩቱ 7 ላቦራቶሪዎች በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪዎች የጥራት ማረጋገጫ መስፈርት (ISO-15189) በማሟላት በአገር የመጀመሪያ የሆነውን ሙሉ እውቅና በማግኘት እና ለ3 ዓመታት እንዳስቀጠለ ገልጸው ይህን እንዲሳካ የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ለነበራቸው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ሰዉ ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰታቸዉንና በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸዉ ተቋማትና ተፈናቃዮች ተቋሙ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት 3 አዳዲስ ቅርንጫፎች ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተው በስራ ላይ መተባበር፣ በስነ-ልቦና ከፍ ብለን መስራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ዕቅዳቸንን በማሳካት ውጤት የምናስመዘግብበት ዓመት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ በአቶ ለዓለም ገደፋዉ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ በ2013 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የምርምር የእዉቀት ሽግግርን ለማሻሻልና መረጃን ለባለድርሻ አካላት ለማሰራጨት የስንቅ ፕሮግራም በየወሩ መካሔዱ፣ ለአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ድጋፍ፣ የህክምና እና ምርመራ አገልግሎት መሰጠት መቻሉ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርመራ ማዕከላትን ማስፋፋትና በተቀናጀ መንገድ መሰራቱ፣ የኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ በሁሉም የላቦራቶሪ ምርመራዎች የጥራት ደረጃውን ማስጠበቁ፣ ሶስት አገር አቀፍና ክልል አቀፍ አጋርነቶችን መመስረት መቻሉ በጥንካሬ ቀርበዋል፡፡ የጥናትና ምርምር ተግባራት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን፣ የላቦራቶሪ መሳሪያ ጥገና ወርክሾፕ ማቋቋም አለመቻሉ፣ አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የጨቅላ ህጻናት መንጋጋ ቆልፍ እና የኩፍኝ አሰሳ ቅኝት ሪፖርት ዝቅተኛ መሆን፣ ከመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የተጠየቁ ግብዓቶችን በወቅቱ አለማግኘት፣ ከክልል እስከ ቀበሌ ካሉ ተቋማት ጋር የሚያስተሳስር የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት አለመኖር እና የተቀናጀ ድጋፋዊ ጉብኝት በእቅዱ መሰረት አለማድረግ በክፍተት ተነስተዋል፡፡ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ በእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ተሰጋ መንግስቱ የቀረበ ሲሆን ዓመታዊ ዕቅዱ ከ10 ዓመቱ ስትራቴጅክ እቅድ የተቀዳ 4 ዓላማዎች፣ 15 የትኩረት አቅጣጫዎች እና 91 አመልካቾችን የያዘ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ ተሰጋ ገለፃ በ2014 በጀት ዓመት በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተደገፈ የጤና ምርምር ልማትን ለማሻሻል፣ ጥራቱ የተረጋገጠ የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠትና የምርመራ አገልግሎት አቅምን ማሻሻል እና የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በተቋሙ በክፍተት የታዩ ተግባራት እንዲጠናከሩ እና ይበልጥ ትኩረት ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ተግባራት ላይ ሃሳብ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን የየክፍል የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት በተቋሙ ተሞክሮ የሚሆኑ በርካታ ስራዎች ማስፋፋት፣ መረጃዎች ማደራጅት እና ዝቅተኛ አፈፃፀሞችን በመለየት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ተቋሙ በክልል አቀፍ ብቻ ሳይሆን በሀገር እና በዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመገንዘብ መደበኛ ስራዎቻችንን ውጤታማ ማድረግ እና ህብረተሰቡን ላይ በመድረስና መሬት የነካ ስራዎችን መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለሕብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ! አሕጤኢ ነሐሴ 3/2013 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *