ኢንስቲትዩቱ 3ኛ ዙር ድጋፉን አደረገ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትህነግ በከፈተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አስተዳደር ዞን ጤና መምሪያ ስር ለሚገኙ ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል ግምታቸው ከ400 ሽህ ብር በላይ የሚያወጡ አንሶላ፣ የፅህፈት መሳሪያ፣ የህክምና ግብዓቶች፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ የቢሮ መገልገያ ወንበርና ጠረንጴዛን ጨምሮ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለዞኑ ጤና መምሪያ ድጋፍ አድርጓል። ኢንስቲትዩቱን ወክለዉ ድጋፉን ያስረከቡት የኢንስቲትዩቱ የዉስጥ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እያደር መለሰ ባለፉት ወራት በአማራነታቸዉ ተፈናቅለዉ በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የአልባሳትና የቁሳቁስ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ኮረም እና ኣላማጣ ሆስፒታሎች የተለያዩ ቁሳቁሶችና የህክምና ግብዓቶችን ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዉ ዛሬ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ተከስቶ በነበረዉ ጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰበት ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ይህ ድጋፍ መደረጉ የጤና ተቋማትን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ታልሞ ኢንስቲትዩቱ ካለው ውስን በጀት በመቀነስ ድጋፉ መደረጉን ገልፀዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ መንገሻ ንጉሡ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት በህግ ማስከበር ዘመቻው በጤና ተቋማት ውድመት፣ የህክምና ቁሳቁሶች የመሰበርና ዝርፊያ የተፈፀመ መሆኑን ገልፀው በዚህ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የበጀት አለመኖር አስቸጋሪ አንዳደረገባቸው ተናግረዋል። አቶ መንገሻ አያይዘውም በዞኑ ካሉት 22 ጤና ጣቢያዎችና 3 ሆስፒታሎች መካከል በሁሉም ጤና ጣቢያዎች የማይክሮስኮፕ መሳሪያዎች ዝርፊያና ስብራት ምክንያት በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ህክምና ለመስጠት መቸገራቸውንና ይህንንም ችግር ለሚመለከተው ተቋም እና አጋር ድርጅቶች ማስታወቃቸውን ገልፀው ችግሩ ግን እስካሁን እንዳልተፈታ ተናግረዋል። በዞኑ ወባ፣ ኩፍኝ እና ውሀ ወለድ በሽታዎች የህብረተሰቡ የጤና ስጋት ተብለው መለየታቸውንና ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት አቶ መንገሻ የውሀ ታንከር እና ውሀ አጋር ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአጋር ድርጅቶች በእርዳታ ማግኘታቸውን ገልፀው አጎበርን በተመለከተ የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተቻለው ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ቃል የተገባላቸው መሆኑን ገልፀዋል። የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች ቸግሩ ተከስቶበት በነበረው ሰአት ከስራ ገበታቸው ለቀው በመሄዳቸው መዋቅሩን ወደ ስራ ለመመለስ የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዞኑ ስር ላሉ ጤና ተቋማት ባለሙያዎች ሙሉ ስልጠና በመሰጠቱ ወደ ተግባር እንደተገባና ሳምንታዊ ሪፖርት መላክ መጀመሩን ገልፀዋል። የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ካሁን ቀደም ካደረገላቸው የባለሙያ ስልጠና ድጋፍ በተጨማሪ ዛሬ የቁሳቁስ እና የህክምና ግብአት ድጋፍ በተመለከተ መምሪያ ሀላፊው ኢንስቲትዩቱ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ ሁሉ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ህዝብ እና በጤና መምሪያው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *