የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “የኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተግባራት የንቅናቄ መድረክ” ከጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ አጋር ድርጅቶች፣ በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በባህርዳር ከተማ ክልል ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ታህሳስ 19/2013 ዓ.ም ተካሄደ፤

የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ማህበረሰባችን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በሚደረገዉ ጥረት ከኪስ በሚወጣ ወጭ ለድህነት እንዳይዳረግ መከላከልና የጤና መድን አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከ10 ዓመት በፊት በጥቂት ወረዳዎች በሙከራ የተጀመረዉ የጤና መድን ዛሬ ላይ በሃገራችን 770 በሚሆኑ ወረዳዎች ከ32 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አባል እንደሆኑና አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል፡፡ ነባር አባላት እድሳት እንዲያደርጉና አዳዲስ አባላት ወደ ማዕቀፉ እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ እንደ ሃገር ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ በሁሉም ከፍተኛ ርብርብ የመከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸዉን የገለፁት ሚንስትሯ የመከላከል ስራዎች በመቀዛቀዛቸዉ በየቀኑ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎች እየበዙ መሆኑንና ሁላችንም በባቤትነት ይዘን በጋራ የወረርሽኙ ስጋትነት እስከሚወገድ ድረስ አጠናክረን ልንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸዉ እንደ ሌሎች ሃገሮች ሁሉ ወረርሽኙ በክልላችን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች ማስከተሉን ገልፀዉ ወረርሽኙን ለመከላከል ከክልል እስከ ቀበሌ አደረጃጀቶች ተዘርግተዉ ተግባራት ሲከወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችና አመለካከቶች በማህበረሰቡ ዉስጥ ይስተዋላሉ ያሉት አቶ አገኘሁ በትኩረት ልንነጋገርበትና ልንመካከርበት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አመራሩና የጤና ባለሙያዉ በህግ የማስከበር ዘመቻ ያደረገዉን ትግል ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላልና ለመቆጣጠር ራሱን ቤተሰቡንና ህብረተሰቡን እንዲታደግ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ አቶ አገኘሁ አያይዘዉም ኮሮናን ከመከላከል ተግባራት ጎን ለጎን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎትን ማሻሻል ለነገ የሚባል ተግባር ባለመሆኑ ህብረተሰባችንን ከድንገተኛ ወጭ መታደግ ይገባል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ እንዳሉት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በህብረተሰቡ ዉስጥ እየታየ ያለዉ ከፍተኛ መዘናጋትና መቀዛቀዝ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ፣ ከዚህም አልፎ አሁን ባደጉ ሃገራት አዲስ የቫይረስ ዝርያ በመከሰቱና ከዚህ በፊት ከነበረዉ ቫይረስ በተለየ ፈጣን በሆነ መንገድ የሚዛመት እንደሆነ የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ሀገራት መረጃዎች በመገኘታቸዉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብና ድጋፍ በማድረግ የወረርሽኙን ስርጭት መግታት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ፎቶ ኢግዚቢሽን ቀርቦ በተሳታፊዎች የተጎበኘ ሲሆን በመድረኩም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት የእዉቅና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *