-የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን መደበኛ ስራዎች በቅንጅት መሰራት እንዳለባቸዉ ተገለፀ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ሃምሌ 25/2012 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ተካሄደ፡፡ በመድረኩ መከፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ኃይሌ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ጎን ለጎን መደበኛ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ያቀረቡት የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ባለሙያዉ አቶ ተመስገን አንተዬ እንደተናገሩት የዚህ መድረክ ዓላማ በ2012 በጀት ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን ለማየትና ለማረም፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመዉሰድ ለ2013 በጀት ዓመትና ለቀጣዩ የተቋሙ ስትራቴጅክ እቅድ ዘመን በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል እንዲሁም ለህብረተሰቡ ጤና መሻሻል የተቋሙ ሚና ምን እንደሚመስል ለማየት ነዉ ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካካል የምርምር መመሪያዎች መዘጋጀታቸዉና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች 5 ምርምሮች መሰራታቸዉ፣ ምርምሮችን ገምግሞ የማፅደቅ፤ የምርምር ምክረ ሃሳቦችን ግብረ መልስና የትብብር ደብዳቤ በመስጠት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ፣ በወባ በሽታ የሚሞቱ ሰዎችን ምጥንነት ከ100,000 ከ1 በታች ማድረስ መቻሉ፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማሰተባበሪያ ማዕከላትን ማሰፋፋት መቻሉ፣ ላብራቶሪዎች የማይሰሯቸውን ናሙናዎች ወደ ተሻለ የምርመራ አገልግሎት ወደሚያገኙበት እንዲልኩ ማስተሳሰር ለሁሉም ላቦራቶሪዎች በፖስታ የታገዘ የላቦራቶሪ የውጤት መላኪያ ዘዴ መዘርጋቱ፣ ላቦራቶሪዎች አሁን ያገኙትን ደረጃ ጠብቀው እንዲቆዩ ድጋፍና ክትትል መደረጉ የሚሉት ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ያገኘዉን የላቦራቶሪ ሙሉ እዉቅና ማስቀጠል መቻሉ፣ በሚዲያዎች መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች፣ የወረርሽ ጭምጭምታዎችን ፈጥኖ ማረጋገጥና ምላሽ መስጠት የመሳሰሉት በጥንካሬ ከተነሱት መካከል ሲሆኑ በተቋሙ የሚሰሩ ምርምሮች በተቀመጠላቸዉ የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ የኮቪድ-19 ምርመራ መጠን አነስተኛ መሆኑ፣ በኤሌክትሮኒክስ ኢንፎርሜሽን ስርዓት የተደራጁ (equipped) ላቦራቶሪዎች መፍጠር አለመቻሉ፣ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች የግብዓት እጥረት መኖር፣ የወረርሽኞች በተደጋጋሚ መከሰትና ለረጅም ጊዜ መቆየት፣ ለዉጭ ጥራት ቁጥጥር ማዕከላት ድጋፍና ክትትል አለመደረጉ የመሳሰሉት በአሰራር ያጋጠሙ ችግሮች ተግባራትን በእቅዱ መሰረት እንዳይፈፀሙ ማድረጋቸዉ ተገልጿል፡፡ በሃይል መቆራረጥ፣ የምርመራ ኪት እጥረት በመሳሰሉት ችግሮች የኮቪድ ምርመራ መጠን አነስተኛ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በዉጤት የታጀበ የተሻለ ስራ ሰርተን አሳይተናል፣ ብለዋል ዶ/ር ማህተመ፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ትኩረታችን ኮቪድ-19 ስራ ላይ የነበረ በመሆኑ በቀጣይ ከኮቪድ ስራ በተጨማሪ ተቋሙ አግኝቶ የነበረዉን ዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ ሙሉ እዉቅና ለማሰቀጠል በሚሰራ ስራ ላይ፣ የዉጭ ጥራት ቁጥጥር ስራዎች እና የመሳሰሉት ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል ዶክተር ማህተመ፡፡ አህጤኢ 27/11/2012 ዓ.ም
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *