የዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 በሚል የንቅናቄ ዘመቻ በአማራ ክልል ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለፀ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተቀዛቀዘ የመጣዉን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፀጥታ ተቋማት እና ከተለያዩ ቢሮዎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ የኮቪድ መከላከያ መንገዶች አተገባበርን በተመለከተ ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 የንቅናቄ ዘመቻ ለማስጀመር የምክክር መድረክ በደብረ ታቦር ከተማ ግንቦት 7/2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ሰብሳቢ እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ክብርት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንደተናገሩት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በክልላችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ቢሆንም በተቃራኒዉ መከላከሉ ላይ ባለዉ መዘናጋት ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በንቅናቄ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል ላይ በማተኮር ህብረተሰቡን በማስተማር፣ ህግን በማስከበር እና የክልሉን የክትባት አፈፃፀም ከፍ ለማድረግ በቀጣይ 2 ወራ ትኩረት ተሰጥቶ በተጠናከረ መንገድ ለመስራት እያንዳንዱ ተቋም ለተግባራዊነቱ ተልዕኮዉን በመዉሰድ የመከላከያ መንገዶችን ለማስተግበር መመሪያ ቁጥር 30/2013 በዘመቻ መጀመር እንዳለበት እና ከሌሎች ተግባሮች ጋር አቀናጅቶ ማስኬድ ይገባል ብለዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ኮቪድ በክልላችን ተከስቶ በነበረበት ወቅት መጠነ ሰፊ ተግባራት በመከናወናቸዉ የተፈራዉን ያህል ጫና ሳያሳድር መቀነስ ተችሎ የነበረ መሆኑን አዉስተዉ አሁን ባለዉ የመከላከያ መንገዶች አፈፃፀም ትግበራ ዝቅተኛ በመሆኑ የበሽታዉ ስርጭት እየተስፋፋ፣ የሚያዙት ሰዎች፣ የፅኑ ህሙማን ቁጥርና የሞት ምጣኔ እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶክተር መልካሙ አያይዘዉም ወረርሽኙ በዚህ ከቀጠለ በክልላችን ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር በመሆኑም የመከላከያ መንገዶች እንደተጠበቁ ሆኖ የኮቪድ መከላከያ ክትባቱን መከተብና ስለ ክትባቱ ጠቀሜታ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመድረኩ ክልላዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ፣ ከህግ አንፃር የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 እና ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋማት ተልዕኮ በተመለከተ መወያያ ፅሁፎች ቀርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ስርጭቱን መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንደሚያስፈልግና በኮቪድ መከላከልና መቆጣጠር ስራችን የነበሩብንን ክፍተቶች በማረም ጠንካራ ጎኖችን አጠናክረን ህብረተሰባችንን ከቫይረሱ መጠበቅ አለብን ካሉ በኋላ የህብረተሰቡንም ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በመመሪያዉ መሰረት ወደ ህግ ማስከበር ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ወረርሽኝን ለመከላከልም ሆነ በሌሎች ተግባራት በአንድነት የሚጠበቅብንን ካልሰራን ዉጤት ማምጣት እንደማይቻልና ሁሉም ተቋማት በኮቪድ መከላከል ተግባርን ወስደዉ መስራት እንደሚጠበቅባዉም አሳስበዋል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ሰራተኞቹንና ደንበኞቹን ከኮቪድ የመከላከል ኃላፊነት አለበት ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ለዚህም የመንግስት ተቋማት አርዓያ በመሆን መከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንደ ሀገር የሚጠበቅባቸዉን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ዶክተር ሙሉነሽ ከምርጫ ስራ ጋር በተገናኘ በሽታዉ ወደ ገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል እንዳይዛመት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባና ከግንቦት 12/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የክልላችን ከተሞች በተመሳሳይ ቀን የዳግም ትኩረት የኮቪድ-19 መከላልና መቆጣጠር ዘመቻ ተፈፃሚ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!!
Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *