ኢንስቲትዩቱ 2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ነሐሴ 1/2013 ዓ.ም አካሄደ፡፡ በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የኢንስቲትዩቱ 7 ላቦራቶሪዎች በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪዎች የጥራት ማረጋገጫ መስፈርት (ISO-15189) በማሟላት በአገር የመጀመሪያ የሆነውን ሙሉ እውቅና በማግኘት እና ለ3 ዓመታት እንዳስቀጠለ ገልጸው ይህን እንዲሳካ የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ለነበራቸው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ሰዉ ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰታቸዉንና በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸዉ ተቋማትና ተፈናቃዮች ተቋሙ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት 3 አዳዲስ ቅርንጫፎች ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተው በስራ ላይ መተባበር፣ በስነ-ልቦና ከፍ ብለን መስራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ዕቅዳቸንን በማሳካት ውጤት የምናስመዘግብበት ዓመት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ በአቶ ለዓለም ገደፋዉ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ በ2013 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የምርምር የእዉቀት ሽግግርን ለማሻሻልና መረጃን ለባለድርሻ አካላት ለማሰራጨት የስንቅ ፕሮግራም በየወሩ መካሔዱ፣ ለአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ድጋፍ፣ የህክምና እና ምርመራ አገልግሎት መሰጠት መቻሉ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርመራ ማዕከላትን ማስፋፋትና በተቀናጀ መንገድ መሰራቱ፣ የኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ በሁሉም የላቦራቶሪ ምርመራዎች የጥራት ደረጃውን ማስጠበቁ፣ ሶስት አገር አቀፍና ክልል አቀፍ አጋርነቶችን መመስረት መቻሉ በጥንካሬ ቀርበዋል፡፡ የጥናትና ምርምር ተግባራት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን፣ የላቦራቶሪ መሳሪያ ጥገና ወርክሾፕ ማቋቋም አለመቻሉ፣ አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የጨቅላ ህጻናት መንጋጋ ቆልፍ እና የኩፍኝ አሰሳ ቅኝት ሪፖርት ዝቅተኛ መሆን፣ ከመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የተጠየቁ ግብዓቶችን በወቅቱ አለማግኘት፣ ከክልል እስከ ቀበሌ ካሉ ተቋማት ጋር የሚያስተሳስር የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት አለመኖር እና የተቀናጀ ድጋፋዊ ጉብኝት በእቅዱ መሰረት አለማድረግ በክፍተት ተነስተዋል፡፡ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ በእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ተሰጋ መንግስቱ የቀረበ ሲሆን ዓመታዊ ዕቅዱ ከ10 ዓመቱ ስትራቴጅክ እቅድ የተቀዳ 4 ዓላማዎች፣ 15 የትኩረት አቅጣጫዎች እና 91 አመልካቾችን የያዘ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ ተሰጋ ገለፃ በ2014 በጀት ዓመት በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተደገፈ የጤና ምርምር ልማትን ለማሻሻል፣ ጥራቱ የተረጋገጠ የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠትና የምርመራ አገልግሎት አቅምን ማሻሻል እና የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በተቋሙ በክፍተት የታዩ ተግባራት እንዲጠናከሩ እና ይበልጥ ትኩረት ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ተግባራት ላይ ሃሳብ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን የየክፍል የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት በተቋሙ ተሞክሮ የሚሆኑ በርካታ ስራዎች ማስፋፋት፣ መረጃዎች ማደራጅት እና ዝቅተኛ አፈፃፀሞችን በመለየት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ተቋሙ በክልል አቀፍ ብቻ ሳይሆን በሀገር እና በዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመገንዘብ መደበኛ ስራዎቻችንን ውጤታማ ማድረግ እና ህብረተሰቡን ላይ በመድረስና መሬት የነካ ስራዎችን መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለሕብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ! አሕጤኢ ነሐሴ 3/2013 ዓ.ም
10

በራንች/ቻግኒ የተፈናቃዎች ጣቢያ ሲሰቱ ለነበሩ የጤና ባለሙያዎች እና ጤና ተቋማት የእዉቅናና የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አዳጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለዉ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ ከህዳር እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም በራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለዉ ለነበሩ ከ 79041 በላይ ተፈናቃዮችን የጤና አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ 32 የጤና ባለሙያዎች እና 3 የጤና ተቋማት (የቻግኒ ሆስፒታል፣ ቻግኒ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እና ቻግኒ ጤና ጣቢያ) የእዉቅናና የምስጋና ፕሮግራም ሃምሌ 3/2013 ዓ.ም አካሄደ፡፡ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አምሳሉ በፕሮግራሙ ላይ ሰብዓዊነት የተሞላበት እና ከየትኛዉም የመደበኛ ስራዎች ጋር የማይነፃፀር አገልግሎት ሰጥታችኋል፤ ለህዝባችሁ ወገንተኝነትን አሳይታችኅል፤ ቤታችሁንም ትታችሁ ለተፈናቃዮች አገልግሎት ስለሰጣችሁ ላቅ ያለ ምስጋና ያስፈልጋችኋል ብለዋል፡፡ አቶ አብርሃም አያይዘዉም በርካታ ችግሮች ገጥመዉን የነበረ ቢሆንም በነበረዉ የተጠናከረ የትብብር ስራ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት ዞን የመመለስ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በራንች የመጠለያ ጣቢያም ደመወዝ የሌላቸዉ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ጭምር የጤና አገልግሎት ሲሰጡ ከርመዋል ብለዋል፡፡ በራንች /ቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ላይ ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማሳለጫ ማዕከል/Osite PHEOC/ አቋቁሞ የጤና ባለሙያዎችን፣ መኪና እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመመደብ ለ8 ወር ያክል ምላሽ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ይህ አይነቱ አሰራርም ለተፈናቃዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለን የአሰራር ዘዴ በመሆኑ በምርጥ ተሞክሮነት ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ከኢንስቲትዩቱ በኩል ተመድበዉ በራንች የተፈናቃዮች ጣቢያ ሲሰሩ በቆዩት ባለሙዎች (አቶ ተፈራ አለሙ እና በአቶ አበበ ሲሳይ) ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ለተፈናቃዮች ሲሰጥ የነበረዉ የጤና አገልግሎት በ4 ዋና ዋና አምዶች የተደራጀ ሲሆን እነሱም፡- የታመሙ ሰዎችን የማከም፣ የግልና የአካባቢን ንፅህና የመጠበቅ፣ የህብረተሰብ ጤና ቅኝት እና የጤና አጠባበቅ ትምህርት ናቸዉ ብለዋል ባለሙያዎች፡፡ ከዚህም ባለፈ የጤና ቡድኑ የምግብ ስርጭቶችን እና የተፈናቃዮችን መረጃ የማጥራት ስራዉን ሲደግፍና ሲያግዝ ነበር ብለዋል አቶ ተፈራ፡፡ እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ እንደዚህ ዓይነት የህብረተሰብ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሁሉንም ሴክተር መስሪያ ቤቶችን እና ሁሉንም የመንግስት የአስተዳደር እርከኖችን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማሳለጫ ማዕከል/EOC/ECC/ ማቋቋም አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡
d

ኢንስቲትዩቱ ክልል አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የባለሞያዎች የንቅናቄ መድረክ አካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክልል አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የባለሞያዎች የንቅናቄ መድረክ ከሰኔ 5 እስከ 6/2013 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ አካሄዷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለፁት ባለፉት 9 ወራት በክልሉ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም፣ ወደፊት የሚፈጠሩ ክስተቶችን በተጠናከረ መንገድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በሀገር ደረጃ ብሎም በክልላችን የተጀመረዉን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ንቅናቄ ዘመቻ ላይ በመወያየት የመድረኩ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባለሞያዎች በማይመች ሁኔታም ዉስጥ ሆነዉ ሞያዊ ሃላፊነታቸዉን ለመወጣት እያከናወኑት ያሉ ተግባሮችን ከመቸዉም ጊዜ በላይ በማስቀጠል ለዉጥ በሚያመጣ መልኩ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር የተከናወኑ ተግባራት በኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የስጋት ተግባቦት ኬዝ ቲም አስተባባሪ በአቶ አሌ አያል እንዲሁም ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 የንቅናቄ ዕቅድ የሕብረተሰብ ጤና ቅኝት ኦፊሰር በአቶ ተስፋሁን ታደገ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የሚመለከታቸዉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አምሳሉ በበኩላቸው ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ እንዲሁም በድጋፋዊ ጉብኝት በሁሉም ወረዳዎች መድረስ ስለማይቻል በየደረጃው ያለው መዋቅር የመደገፍና የማብቃት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በማጠቃለያዉ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁት እንደ ክልል የሃገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን፤ በግጭት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸዉ ጤና ተቋማት እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ ዞኖች እና ወረዳዎች ተናበዉ በመስራት ሕብረተሰቡን ማገልገል ሙያዊ ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባ እና የኮቪድ መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ስልቶችን በእቅዱ መሰረት በዉጤታማነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ሌሎች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የአብክመ ጤና ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸዉ በጤና ተቋማት የሚነሳዉ የሰዉ ሃይል፣ የመዋቅርና የደረጃ ጥያቄዎች ቢሮዉ ለመፍታት በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የስራ ላይ ስልጠናዎች መጠናከር እንዳለባቸዉ ይሁን እንጂ ሁሉንም የክልሉ ባለሞያዎች ማሰልጠን አቅም የማይፈቅድ በመሆኑ ስልጠና ያገኙት እዉቀትና ልምድ በማሸጋገር ረገድ ያለዉ ክፍተት መስተካከል እንዳለበት አቶ አብዱልከሪም ጠቁመዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት ዶክተር የሻምበል አጉማስ “እስኪሆን የመፋለም ቀመር ወቤተ ሙከራ” በሚል ርዕስ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ መድረኩ በ2 ዙር የተካሄደ ሲሆን የኢንስቲትዩቱና የጤና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣ አጋር አካላት፣ የዞንና የወረዳ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያዎች ከ 500 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!! አሕጤኢ 6/10/2013 ዓ.ም

የጤና መረጃን ለፖሊሲ (Evidence To Policy) በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ፤

የጤና መረጃን ለፖሊሲ (Evidence To Policy) በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ፤ በአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከፍኖተ ሃርቫርድ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የጤና መረጃን ለፖሊሲ (Evidence To Policy) በሚል ርዕስ ለምርምርና የእዉቀት ቋት አባላት (Knowledge Hub Members) መረጃን እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸዉ አቅም ለማጎልበት እና የተመራማሪዎችና የፕሮግራም ሰዎች በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚያስችል ስልጠና በባህርዳር ከተማ ተሰጥቷል፡፡ በስልጠናዉ መክፈቻ ላይ የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደተናገሩት የጤና ምርምርና ልማት በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለ እና ማደግ ያለበት የስራ ክፍል መሆኑን ጠቅሰዉ ከተሰጠዉ ዋነኛ ሃላፊነት የጤና ምርምር ልማትን ማጠናከር እና ማጎልበት መሆኑም ገልፀዉ ዩኒቨርሲቲዎችን እና አጋር አካላት በጋራ በመሆን ይህንን የስራ ዘርፍ ማጠናከርና የጤና ሴክተሩን ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች መዘጋጀታቸዉ ጠቀሜታቸዉ የጎላ ነዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፍኖተ ሃርቫርድ ፕሮጀክት በጤና ፕሮግራም ላይ የሚሰሩ ተመራማሪዎችን በአንድ ላይ በማገናኘት የምርምር ሃሳቦችን መቀያየርና ችግሮችን አብሮ መፍታት እና መረዳዳት ተግባራት ላይ ካሁን በፊት መድረኮች መካሄዳቸዉን አዉስተዉ ምርምሮች በዩኒቨርሲቲዎች እና በሌሎችም ደረጃ እየተሰሩ ቢሆንም ጤና ፕሮግራሞች ግን እየተጠቀሙባቸዉ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ጥናቶቹ ጥቅም ላይ ቢዉሉ ለዉጥ ማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የጤና ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታየ ዘሩ በበኩላቸዉ የፍኖተ ሃርቫርድ ፕሮጀክት እያደረገላቸዉ ላለዉ ትብብርና ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ካሁን በፊት ከፕሮጀክቱ ጋር በተደረገ የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዉ የምርምር የእዉቀት ቋት አባላት/Knowledge Hub Members) በተቀመጠላቸዉ የአሰራር ስርዓት መሰረት ጠንክረዉ እንዲሰሩና ወደ ፊት ለሚሰሩ ስራዎች የድርጊት መርሃ ግብር ወጥቶላቸዉ ወደ ተግባር እንዲገባ አሳስበዋል፡፡ የስልጠናዉ ተሳታፊዎችም ከስልጠናዉ ጥሩ ግብዓት ያገኙ መሆኑን፣ የሚሰሩ ጥናቶች የፖሊሲ ክፍተት ያለባቸዉ በመሆናቸዉ መስተካከል እንደሚገባዉ፣ የሚጠኑ ጥናቶች አካባቢያዊ ጥናቶች እንዲሆኑ እና ለቀጣይ ስራዎች የድርጊት መርሃ ግብሮች ሊቀመጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በወርክሾፑ ከፍኖተ ሃርቫርድ፣ በክልሉ ካሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከግል ጤና ተቋማት የተዉጣጡ የእዉቀት ቋት አባላት ተሳትፈዋል፡፡ አሕጤኢ

ኢንስቲትዩቱ 3ኛ ዙር ድጋፉን አደረገ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትህነግ በከፈተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አስተዳደር ዞን ጤና መምሪያ ስር ለሚገኙ ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል ግምታቸው ከ400 ሽህ ብር በላይ የሚያወጡ አንሶላ፣ የፅህፈት መሳሪያ፣ የህክምና ግብዓቶች፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ የቢሮ መገልገያ ወንበርና ጠረንጴዛን ጨምሮ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለዞኑ ጤና መምሪያ ድጋፍ አድርጓል። ኢንስቲትዩቱን ወክለዉ ድጋፉን ያስረከቡት የኢንስቲትዩቱ የዉስጥ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እያደር መለሰ ባለፉት ወራት በአማራነታቸዉ ተፈናቅለዉ በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የአልባሳትና የቁሳቁስ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ኮረም እና ኣላማጣ ሆስፒታሎች የተለያዩ ቁሳቁሶችና የህክምና ግብዓቶችን ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዉ ዛሬ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ተከስቶ በነበረዉ ጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰበት ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ይህ ድጋፍ መደረጉ የጤና ተቋማትን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ታልሞ ኢንስቲትዩቱ ካለው ውስን በጀት በመቀነስ ድጋፉ መደረጉን ገልፀዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ መንገሻ ንጉሡ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት በህግ ማስከበር ዘመቻው በጤና ተቋማት ውድመት፣ የህክምና ቁሳቁሶች የመሰበርና ዝርፊያ የተፈፀመ መሆኑን ገልፀው በዚህ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የበጀት አለመኖር አስቸጋሪ አንዳደረገባቸው ተናግረዋል። አቶ መንገሻ አያይዘውም በዞኑ ካሉት 22 ጤና ጣቢያዎችና 3 ሆስፒታሎች መካከል በሁሉም ጤና ጣቢያዎች የማይክሮስኮፕ መሳሪያዎች ዝርፊያና ስብራት ምክንያት በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ህክምና ለመስጠት መቸገራቸውንና ይህንንም ችግር ለሚመለከተው ተቋም እና አጋር ድርጅቶች ማስታወቃቸውን ገልፀው ችግሩ ግን እስካሁን እንዳልተፈታ ተናግረዋል። በዞኑ ወባ፣ ኩፍኝ እና ውሀ ወለድ በሽታዎች የህብረተሰቡ የጤና ስጋት ተብለው መለየታቸውንና ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት አቶ መንገሻ የውሀ ታንከር እና ውሀ አጋር ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአጋር ድርጅቶች በእርዳታ ማግኘታቸውን ገልፀው አጎበርን በተመለከተ የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተቻለው ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ቃል የተገባላቸው መሆኑን ገልፀዋል። የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች ቸግሩ ተከስቶበት በነበረው ሰአት ከስራ ገበታቸው ለቀው በመሄዳቸው መዋቅሩን ወደ ስራ ለመመለስ የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዞኑ ስር ላሉ ጤና ተቋማት ባለሙያዎች ሙሉ ስልጠና በመሰጠቱ ወደ ተግባር እንደተገባና ሳምንታዊ ሪፖርት መላክ መጀመሩን ገልፀዋል። የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ካሁን ቀደም ካደረገላቸው የባለሙያ ስልጠና ድጋፍ በተጨማሪ ዛሬ የቁሳቁስ እና የህክምና ግብአት ድጋፍ በተመለከተ መምሪያ ሀላፊው ኢንስቲትዩቱ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ ሁሉ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ህዝብ እና በጤና መምሪያው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተቀዛቀዘውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተግባራት እንደገና ለማነሳሳት የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ፤

በአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት(አሕጤኢ) ከክልሉ የጤና ቢሮ እና ከክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ሃይል ጋር በመተባበር የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልል ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ግንቦት 04/2013 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ የንቅናቄ መድረክ ተካሄዷል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ሰብሳቢ እና ከክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ሃይል አስተባባሪ ክብርት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደረናገሩት የኮሮና መከላከያ መንገዶችን ባለመተግበራችን በክልላችን የሚያዘው፣ በፅኑ ህመም ያለው እና የሚሞተው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነና መከላከያ መንገዶች በመተግበር እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን መስራት አለበት ብለዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እና የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በክልላችን ከ262 ሽህ በላይ ምርመራ ተደርጎ ከ10 ሽህ 8 መቶ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እንደተያዙ እና 2 መቶ 50 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ ተናግራዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 894 ሽህ 7 መቶ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ እና እየተሰጠ ያለውን ምላሽ፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲሁም የቀጣይ 2 ወር የንቅናቄ ዕቅድን አብራርተዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ በወጣው መመሪያ 30/2013 ን ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ መስሪያ ቤት የህግ ምክር ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሴ ስዩም ሲሆኑ መመሪያውን ጥሰው የተገኙ ሰዎች በአገሪቱ የወንጀል ህግ መሰረት ከቀላል እስከ ዕድሜ ክል ፅኑ እስራት እና በገንዘብ እንዲሁም ያላስፈፀሙ ሃላፊዎች ደግሞ በፀረ-ሙስና በመከሰስ እንደሚቀጡ የተደነገገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመድረኩ የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የመከላከል ስራዎችን በመስራት ህይወትን ወደነበረት ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እንደነበር የተናገሩት የአብክመ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ አሁን አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመከላከል ስራው የተተወ በመሆኑ ዳግም ትኩረት ለኮቪ-19 በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ንቅናቄ በክልላችንም ተግባራዊ ብለዋል፡፡ ዶክተር ሙሉነሽ በማጠቃለያ ንግግራቸው መጀመሪያ ራሳችን አርአያ ሁነን በመገኘት እንደ ግለሰብ እና እንደተቋም በመዋቅራቸሁ መሰረት ወደ ዞንና ወረዳ በማውረድ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት እና የወጣውን ህግም ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ በምርጫው ወቅት የኮቪድ 19 መከላከያን መንገዶችን አቀናጅቶ መስራት፣ ሚዲያዎች ህብረተሰቡን የማስተማር ስራን በሰፊው መስራት እንዳለባቸው ተናግረው እንደ አገር የተደቀኑብንን ችግሮች በጋራ አንድ ሁነን ካለፍናቸው ታሪክ ሰሪ ትውልድ መሆን እንችላለን፡፡

ኢንስቲትዩቱ ድጋፉን አጠናክሮ እየቀጠለ ነዉ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች የኢትዮጵያዊነት መለያ ባህሪ የሆነዉን መተሳሰብ፣ መደጋገፍና አብሮ የመኖር እሴት በተግባር ለመግለፅ ተቋሙ ካለዉ ዉስን ሃብትና በጀት በመቀነስ እንዲሁም ከተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዝ በመቀነስ አማራ በመሆናቸዉ ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲያደርግ የነበረዉን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል ዛሬም በአላማጣና ኮረም ከተማ አስተዳደሮች ስር ለሚገኙ አገልግሎት ሰጭ የመንግስት ሆስፒታሎች ግምታቸዉ ከ250ሽህ ብር በላይ የሚያወጡ የፅህፈት መሳሪያ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ፣ ዲስክቶፕ ኮምፒዩተር፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ለአንቡላንስ አገልግሎት የሚዉል የነዳጅ ኩፖን እና የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን በማስረከብ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡ ትህነግ የአማራን ህዝብ ለማጥፋት ጦርነት ቢያዉጅም በከፈተዉ ጦርነት ራሱ ከስር መሰረት ተነቅሎ በአማራነት ጥያቄያቸዉ መልስ ላገኙ የኮረምና የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታሎች የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ቋሚ እና አላቂ እንዲሁም የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን ድጋፍ ለማድረግ መገኘታቸዉንና ቀጣይም ድጋፍና ክትትሉ እንደሚቀጥል የድጋፉ አስተባባሪ አቶ እያደር መለሰ በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል፡፡ በርክክቡ ላይ የኮረም ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ገብረ ሚካኤል ታፈረ ሆስፒታሉ ከነ ችግሮቹም ቢሆን ሙሉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በአሰራር ላይ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር፣ የባለሙያ እጥረት፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ ባለፉት 8 ወራት እየተከፈለ አለመሆኑ እንደ ችግር አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረገላቸዉ ድጋፍም ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ወሳኝ በሆነ ሠዓት ድጋፉ በመድረሱ ትልቅ መፍትሄ መሆኑንና የተደረገዉ ድጋፍ ለአገልግሎት አሰጣጡ መቀላጠፍ ወሳኝ ሚና ያለዉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መክተ አበበ በበኩላቸዉ አሁን ላይ ተጠሪነታቸዉን አዉቀዉ ችግራቸዉን አቅርበዉ አድማጭ ማግኘታቸዉንና ሪፖርት ለአማራ ክልል እየላኩ መሆኑንና በተደረገላቸዉ ድጋፍ የተሰማቸዉን ሃሳብ ገልፀዉ ሆስፒታሉ ተጨማሪ ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም ትብብር እንዲያደርጉላቸዉ በአላማጣ ህዝብ ስም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የላቦራቶሪ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ ነዉ ለማለት አያስደፍርም ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ የባለሙያ ጥቅማ ጥቅም ክፍያ መክፈል እንዳልተቻለና ጥያቄዉንም ለዞንና ለክልል ማቅረባቸዉን ይህም የመንግስት አሰራርን ተከትሎ ተፈፃሚ እንደሚሆን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዉ ባለን አቅም ሁሉ የህክምና አገልግሎቱ እንዳይቆራረጥ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ሌላኛዉ አስተያየታቸዉን የሰጡት የአላማጣ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ፈንታ ኢንስቲትዩቱ በአይነት፣ በመጠን እና በይዘት ባደረገላቸዉ ድጋፍ መደሰታቸዉን ገልፀዉ ለተቋሙ የስራ ስልጠት ከፍተኛ ግብዓት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ አማረ ገለፃ ተከስቶ በነበረዉ ጦርነት ወቅት ሆስፒታሉ ቀንና ሌሊት ህብረተሰቡን ያገለግል እንደነበረ ገልፀዉ ሆስፒታሉ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ዉስጥ ሆኖ የቆየ በመሆኑ የቴስት ኪት መቆራረጥ፣ የተበላሹ ማሽኖች ጥገና አለመደረግ ዩመሳሰሉት ችግሮች እንዳሉባቸዉና እንዲሟሉላቸዉ ጠይቀዋል፡፡ የድጋፉ አስተባባሪም የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የክልሉ ጤና ቢሮ ሆስፒታሎቹ ላነሱት ጥያቄ በሚቻለዉ ሁሉ ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!!

በተደራጀ መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለዉን ህመም፣ ሞት እና አጠቃላይ ቀዉስ መቀነስ እንደሚገባ ተገለፀ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ክልላዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ፣ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 አተገባበርና የቀጣይ 3 ወራት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ሚያዚያ 18/2013 ዓ.ም በደብረታቦር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነና ተከስቶ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በመሰራቱ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ በመሆን እዉቅና መገኘቱን አዉስተዉ አሁን ላይ የምርመራ መጠኑ ቀንሶ የኮሮና ቫይረስ የሚገኝባቸዉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ ነዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቫይረሱ ተይዘዉ ወደ ፅኑ ህሙማን የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተና የሞት ምጣኔዉም እየጨመረ ነዉ ብለዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የመከላከል ስራዎችን በተደራጀ መንገድ ለማስጀመርና የኮቪድ-19 መከላከል ስራን ከመደበኛ ተግባራት ጎን ለጎን ለማስኬድ መመሪያ ወደ ዞንና ወረዳዎች የማዉረድ ስራ መሰራቱንና ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወረርሽኙን ለመከላከልና የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ቅኝት ባለሙያ አቶ ተስፋሁን ታደገ የክልሉን የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታ መወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 17/2013 ዓ.ም ከ 263ሽህ በላይ የላቦራቶሪ ምርመራ እንደተደረገና 10ሽህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተጠቁ፣ 218 ሞት መከሰቱንና የሞት ምጣኔዉም 2.18 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ካሉ 11 የምርመራ ማዕከላት 6ቱ ብቻ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸዉን፣ ክትባት መዉሰድ ካለባቸዉ 77ሽህ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተቋም ሰራተኞች መካከል 32ሽህ የሚጠጉት ብቻ ክትባቱን እንደወሰዱ አቶ ተስፋሁን አክለዉ ገልፀዋል፡፡ እንደ ክልል ለጤና ባለሙያዎችና እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰጠዉ የክትባት መጠን 442ሽህ ዶዝ ቢሆንም መጠቀም የተቻለዉ 53ሽህ 539 ዶዝ (12%) ብቻ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘበናይ ቢተዉ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የተለያዩ ስራዎች መሠራታቸውን ገልፀዉ የኦክስጅን እጥረት፣ ለኮቪድ-19 ፅኑ ህሙማን የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት እንዳጋጠማቸዉ ገልፀዉ የበሽታዉ ስርጭት በመጨመሩ ከሚመረመሩት ውስጥ ከግማሽ በላይ ቫይረሱ እየተገኘባቸዉ መሆኑን፣ የሞት መጠኑም እየጨመረ መሆኑንና ወረርሽኙ ከቁጥጥር ዉጭ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ኮቪድ-19 ላይ ከክልል እስከ ወረዳ መዋቅር ተዘርግቶ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቢቆዩም አሁን ላይ መዋቅሮቹ ላይ መቀዛቀዝ መኖሩ፣ የኮቪድ መከላከያ ዘዴዎች መመሪያ አተገባበር ተፈፃሚ አለመሆኑ፣ የተፈናቃይ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ፣ የመጠለያ ቤት፣ ምግብ ነክ ግብዓቶች እጥረት፣ የኮቪድ መስፋፋት፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የትርፍ ጊዜ ክፍያ፣ የመሳሰሉት እንደ ችግር ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዋለ በላይነህ በዉይይቱ ላይ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎች አፈፃፀም መመሪያን መተግበር የብዙዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ርብርብ እንደሚያስፈልግና የፀጥታ መዋቅሩ የራሱን ድርሻ እንደሚወስድም ተናግረዋል:: በመጨረሻም ኮቪድን በመከላከል ተግባር ሌሎች ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ሁሉም የጤና ባለሙያ አርአያ በመሆን፣ ኮቪድ -19 ክትባቱ መውሠድና ሌሎችም እንዲከተቡ በማድረግ በአጭር ጊዜ አፈፃፀሙን ማሳደግ፣ እንደ ክልል የተጀመረው የኮቪድ መከላከል የቅንጅት ስራ እስከ ታች ጤና ተቋማትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከመደበኛ ስራዎች ጎን ለጎን መከላከሉን ውጤታማ ለማድረግ በተደራጀ መንገድ መስራት ይገባል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ በመድረኩ ከጤና ቢሮ፣ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ የዞን ጤና መምሪያ ሃላፊዎች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆችና ሜዲካል ዳይሬከተሮች፣ በክልሉ የኮቪድ አስተባባሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ አሕጤኢ ሚያዚያ 19/2013 ዓ.ም

የዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 በሚል የንቅናቄ ዘመቻ በአማራ ክልል ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለፀ፤

የአብክመ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተቀዛቀዘ የመጣዉን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፀጥታ ተቋማት እና ከተለያዩ ቢሮዎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ የኮቪድ መከላከያ መንገዶች አተገባበርን በተመለከተ ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 የንቅናቄ ዘመቻ ለማስጀመር የምክክር መድረክ በደብረ ታቦር ከተማ ግንቦት 7/2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ሰብሳቢ እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ክብርት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንደተናገሩት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በክልላችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ቢሆንም በተቃራኒዉ መከላከሉ ላይ ባለዉ መዘናጋት ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በንቅናቄ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል ላይ በማተኮር ህብረተሰቡን በማስተማር፣ ህግን በማስከበር እና የክልሉን የክትባት አፈፃፀም ከፍ ለማድረግ በቀጣይ 2 ወራ ትኩረት ተሰጥቶ በተጠናከረ መንገድ ለመስራት እያንዳንዱ ተቋም ለተግባራዊነቱ ተልዕኮዉን በመዉሰድ የመከላከያ መንገዶችን ለማስተግበር መመሪያ ቁጥር 30/2013 በዘመቻ መጀመር እንዳለበት እና ከሌሎች ተግባሮች ጋር አቀናጅቶ ማስኬድ ይገባል ብለዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ኮቪድ በክልላችን ተከስቶ በነበረበት ወቅት መጠነ ሰፊ ተግባራት በመከናወናቸዉ የተፈራዉን ያህል ጫና ሳያሳድር መቀነስ ተችሎ የነበረ መሆኑን አዉስተዉ አሁን ባለዉ የመከላከያ መንገዶች አፈፃፀም ትግበራ ዝቅተኛ በመሆኑ የበሽታዉ ስርጭት እየተስፋፋ፣ የሚያዙት ሰዎች፣ የፅኑ ህሙማን ቁጥርና የሞት ምጣኔ እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶክተር መልካሙ አያይዘዉም ወረርሽኙ በዚህ ከቀጠለ በክልላችን ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር በመሆኑም የመከላከያ መንገዶች እንደተጠበቁ ሆኖ የኮቪድ መከላከያ ክትባቱን መከተብና ስለ ክትባቱ ጠቀሜታ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመድረኩ ክልላዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ፣ ከህግ አንፃር የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 እና ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋማት ተልዕኮ በተመለከተ መወያያ ፅሁፎች ቀርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ስርጭቱን መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንደሚያስፈልግና በኮቪድ መከላከልና መቆጣጠር ስራችን የነበሩብንን ክፍተቶች በማረም ጠንካራ ጎኖችን አጠናክረን ህብረተሰባችንን ከቫይረሱ መጠበቅ አለብን ካሉ በኋላ የህብረተሰቡንም ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በመመሪያዉ መሰረት ወደ ህግ ማስከበር ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ወረርሽኝን ለመከላከልም ሆነ በሌሎች ተግባራት በአንድነት የሚጠበቅብንን ካልሰራን ዉጤት ማምጣት እንደማይቻልና ሁሉም ተቋማት በኮቪድ መከላከል ተግባርን ወስደዉ መስራት እንደሚጠበቅባዉም አሳስበዋል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ሰራተኞቹንና ደንበኞቹን ከኮቪድ የመከላከል ኃላፊነት አለበት ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ለዚህም የመንግስት ተቋማት አርዓያ በመሆን መከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንደ ሀገር የሚጠበቅባቸዉን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ዶክተር ሙሉነሽ ከምርጫ ስራ ጋር በተገናኘ በሽታዉ ወደ ገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል እንዳይዛመት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባና ከግንቦት 12/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የክልላችን ከተሞች በተመሳሳይ ቀን የዳግም ትኩረት የኮቪድ-19 መከላልና መቆጣጠር ዘመቻ ተፈፃሚ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!!
በደም ዉስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን (Viral load) እና በደማቸዉ ዉስጥ ቫይረሱ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ (EID) ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ፤

በደም ዉስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን (Viral load) እና በደማቸዉ ዉስጥ ቫይረሱ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ (EID) ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ፤

የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (አሕጤኢ) የህክምና ላቦራቶሪ ዳይሬክቶሬት በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ በ8 ወራት በደም ዉስጥ ያለዉን የኤች አይቪ ቫይረስ መጠን (Viral load) እና ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት (EiD) ምርመራ ላይ የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በክልሉ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት (ART) የሚከታተሉ ሰዎች በተለያየ ምክንያት በደማቸዉ ዉስጥ ያለዉ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን ምርመራ በተሟላ ሁኔታ እየተሰራላቸዉ አለመሆኑንና ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ መሰራት የሚገባዉ ቢሆንም በተፈለገዉ ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቅሰዉ በነዚህ ተግባራት ስኬታማ መሆን ካልተቻለ ሊያስከትል የሚችለዉ ችግር ከፍተኛ ነዉ ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ለዝቅተኛ ተግባራት አፈፃፀም ምክንያቶችን ለይቶ በፍጥነት እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ በመግባት ከፍተኛ ለዉጥ ማምጣት ይገባል ካሉ በኋላ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያም የዳበረ ንቃተ-ህሊና ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአማራ ክልል የሲዲሲ ፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ መሰረት አዲሱ በክልሉ ያለዉን የ8 ወር የኤች.አይ.ቪ መከላከልና መቆጣጠር ስራ በጤና ተቋማት ያለዉን አፈፃፀም ምን እንደሚመስል በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እየሰጡ መሆኑን፣ 340 የመንግስት 33 የግልና መንግስታዊ ያልሆኑ ጤና ተቋማት ART እየሰሩ መሆናቸዉን እንዲሁም 5 የደም ዉስጥ ያለዉን የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን የሚሰሩ ማዕከላት መኖራቸዉንና 2 ተጨማሪ ማዕከላት (ወልዲያና ደብረታቦር) ስራ ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ መሰረት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ጠቅሰዉ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ በ2021 በክልላችን 208 ሽህ ሰዎች የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ፣ 7ሽህ 499 አዲስ ተጠቂዎች እንዲሁም 3ሽህ 162 በቫይረሱ ምክንያት ዓመታዊ ሞት ሊከሰት እንደሚችልም ተገምቷል ብለዋል፡፡ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ፣ መመርመር ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ቫይረሱ ያለባቸዉ እንደተገኙና ከተገኘባቸዉ ዉስጥም ምን ያህሉ መድሃኒት እንዲወስዱ እንደተደረገ መከታተል እንደሚገባ የተናገሩት ወ/ሮ መሰረት በክልሉ ባለፈዉ 8 ወር 470 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዉ መድሃኒት ማስጀመር እንዳልተቻለ ገልፀዉ ቫይረሱ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ከዓመታዊ ግብ 63.3 በመቶ በመሆኑ ከፍተኛ ስራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በክልሉ ባለፈዉ 8 ወር በ5ቱ በደም ዉስጥ ያለዉን የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን ምርመራ መጠን እና ቫይረሱ በደማቸዉ ካለባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ምርመራ አፈፃፀም፣ በናሙና አላላክ ችግር ምክንያት የሚወገዱ ናሙናዎችን በተመለከተ የኢንስቲትዩቱ የቫይሮሎጅ ላቦራቶሪ ፎካል አቶ ደመቀ እንዳላማዉ አቅርበዋል፡፡ ከተሳታፊዎችም ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተዉ ዉይይት የተደረገ ሲሆን ከተለያዩ ተቋማት የሚመጡ የናሙና መቀበያ ፎርማቶች አንድ ወጥ አለመሆን፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ፣ ፖስታ ቤት ላይ ጠንከር ያለ ስራ አለመሰራቱ፣ የናሙና ጥራት መጓደል፣ የኤች.አይ.ቪ መመርመሪያ ኪት እጥረት፣ የግብዓት እጥረት፣ የመሳሰሉት እንደ ክፍተት ተነስተዋል፡፡ በመድረኩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮ የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ጨምሮ ከተለያዩ ዞኖች የተዉጣጡ ኃላፊዎችና የኤች.አይ.ቪ ኦፊሰሮች፣ የላቦራቶሪ አስተባባሪዎች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ለህብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!! አሕጤኢ 20/7/2013 ዓ.ም