ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ውጭ ጥራት ቁጥጥር(EQA) እና የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ማዕከላት አፈፃፀምን ገመገመ፤

ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ውጭ ጥራት ቁጥጥር(EQA) እና የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ማዕከላት አፈፃፀምን ገመገመ፤

የአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደሴ ቅርንጫፍ የምስራቅ አማራ የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ የውጭ ጥራት ቁጥጥር (EQA) እና የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ማዕከላት አፈፃፀም ግምገማ በደሴ ከተማ አካሂዷል፡፡ በምስራቅ አማራ 31 የውጭ ጥራት ቁጥጥር(EQA) ማዕከላት ያሉ ሲሆን በአቀስታ፣ በአጣዬ እና በቅዱስ ላሊበላ ሆስፒታሎች የ2012 በጀት ዓመት በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ በወባ እና በቲቢ እንዲሁም ወሎና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረ ብርሃን አጠቃላይ ሆስፒታል እና በኢንስቲትዩቱ(ደሴ ቅርንጫፍ) በኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከላት የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የመረጃ አያያዝ ጥራት መጓደል፣ የማሽን ብልሽት፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ ሪፖርት በወቅቱ አለመላክ፣ ድጋፍና ክትትል በወቅቱ አለማድረግ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚሉት ተግባራት በዕቅዱ መሰረት እንዳይፈፀሙ እንደ ችግር በውይይቱ ተነስተዋል፡፡ በመድረኩ የ2013 በጀት ዓመት የጋራ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም ባለሙያ በጋራ መስራት እንዳለበት የአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ አሳስበዋል፡፡ ዶክተር ማህተመ በመድረኩ ማጠቃለያው ላይ እንዳሉት የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን በመቅረፍ፣ ድጋፍና ክትትል ስርዓታችን በማጠናከር እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አውስተው ለህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቅ አገልግሎት ለመስጠት ሃላፊነታችንን በመወጣት በጋራ ለተሻለ ውጤት ለማምጣት መስራት አለብን ብለዋል፡፡ ምስራቅ አማራ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ እና ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞኖች እና ደሴ ከተማ አስተዳደርን የያዘ ነው፡፡
1.	በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታን ለመከላከል ክትባት እንደሚሰጥ ተገለፀ፤

በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታን ለመከላከል ክትባት እንደሚሰጥ ተገለፀ፤

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከህዳር 18 እስከ 21/2013 ዓ.ም በክልሉ የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ ለመከላከል በዘመቻ ክትባት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ አንድ ተጠቂ ላይ የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ ኦሮሞ ብሔረሰብ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ ዞኖችን እና ደሴ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያው ዙር ክትባት ይሰጣል ብለዋል፡፡ በዘመቻው 6 መቶ 65 ሽህ 2 መቶ 84 ህፃናት የክትባት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ክትባቱ የሚሰጠው ቤት ለቤት በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ህጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ህፃን ክትባት ማግኘት እንዳለበት የገለፁት የቢሮው ሃላፊው የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ የቅኝትና የዳሰሳ ስራዎች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በክትባቱ ወቅት የሚሳተፋ ባለሙያዎች እና ወላጆች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ እጅን በውሃና በሳሙና በመታጠብ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ሃላፊው አሳስበዋል። የአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና አሰሳ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አሌ አያል በበኩላቸው ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በመስጠት፣ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራቱን ገልጸው ዘመቻውን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ አካላትን ያካተተ አደረጃጀት መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) በሽታ ክትባት ከ15 ቀናት በኋላ ይካሄደል፡፡
ለአመራርና ለሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ስልጠና ተሰጠ፤

ለአመራርና ለሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ስልጠና ተሰጠ፤

ለአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ህዳር 13/2013 ዓ.ም የመልካም አስተዳደር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት በአቶ የሻምበል አጉማስ “አብርሆተ ሰብእ” በሚል ርዕስ ሲሆን በተቋሙ ያሉ ችግሮችን አስወግዶ በቅንነትና ተሳሰቦ መስራት ተቋማችሁን በመለወጥ አገራችን በአያቶቻችንና በቅድመ አያቶቻችን ወደ ነበረችበት ገናናነት መመለስ እንዳለብን አመላክተዋል፡፡ አቶ የሻምበል አያይዘውም የተቋሙ ሰራተኞች ተደራጅተው በቀላል መዋጮ የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎችን በመስራት ራስን ብሎም አካባቢን መለወጥ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተም ሃይሌ በስልጠናው ላይ እንዳሉት ሁሉም ሰራተኛ ለተመደበበት የስራ ሃላፊነት አመራር መሆኑን አውቆ ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየር እና ለተቋሙ ለውጥ በጋራ በመስራት እንደ ክልል ሞዴል ለመሆን መጣር አለብን ብለዋል፡
የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት የገንዘብ ድጋፍና የደም ልገሳ አደረጉ፤

የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት የገንዘብ ድጋፍና የደም ልገሳ አደረጉ፤

የአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች ህዳር 08/2013 ዓ.ም ባካሄዱት ውይይት ህግን በማስከበር ላይ ለሚገኘው ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት ከተቋሙ በጀት 200,000.00 /ሁለት መቶ ሽህ ብር/ እና የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተም ሃይሌ በውይይቱ ላይ ህግን ለማስከበር ህወታቸውን ሳይሰስቱ የአገር ሰላም እና ደህንነት ለማስከበር በዘመቻ ላይ ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት የተደረገው ድጋፍ ጥሩ መሆኑን አውስተው ወደፊትም አጠናረው መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው በትግራይ ክልል በአገር መከላከያ ላይ የፈፀመውን ድርጊት አውግዘው ይህንን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አካባቢያችንን በጥንቃቄ በመጠበቅ እንዲሁም ሙያቸው የሚፈቅደውን ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢንስትዩቱ አመራርና ሰራተኞች ህወይቱን እየሰዋ የአገር ድንበር ለሚያስከረው ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት ደም ለግሰዋል፡፡
በፖሊዮ ዘመቻ የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ፤

በፖሊዮ ዘመቻ የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተዉጣጡ ባለሙያዎች በፖሊዮ በሽታ ክትባት አሰጣጥ ላይ የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ ተሰጠ፡፡ ስልጠናዉ በቀጣይ በክልሉ በሚካሄደዉ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተግባራት ወቅት የማህበረሰቡን ተሳትፎና ግንዛቤ ለማሳደግ በርካታ የመገናኛ አዉታሮችን እንደ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የጤና ሰራተኞችን በመጠቀም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ ማህበረሰቡን በማስተማር ለማበረታታትና ለማነሳሳት እንዲሁም የባህሪ ለዉጥ እንዲያመጣ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ በማዉጣት ለመተግበር የሚያስችል ነዉ፡፡ የክትባቱን አስፈላጊ፣ የፖሊዮ ዘመቻዉ መቼ እና የት የት አካባቢዎች እንደሚከናወን ለማሳወቅ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊስፋፋ የሚችል ጥርጣሬን ወይም የተሳሳተ ግንዛቤን ለማስወገድ፣ ፖሊዮ በልጆች ላይ ሽባነትን ወይም ሞት ሊያስከትል የሚችል በሽታ መሆኑንና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ልጆች ከዚህ በፊት ክትባቱን ቢወስዱም ባይወስዱም መከተብ እንዳለባቸው መልዕክቶችን በመቅረፅ በድግግሞሽና ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ አዉታሮችን ተጠቅሞ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በዘመቻዉም ባለድርሻ አካላት ማለትም የሃይማኖት መሪዎች፣ የህብረተሰቡ አመራሮች (የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች ፣ የሰፈር ሃላፊዎች፣ የትምህርት ቤት ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞች – ሚዲያ (ቲቪ / ሬዲዮ)፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ በልጆች ጤና እና ትምህርት ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሴቶች እና የወጣት መሪዎችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ፖሊዮ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ፣ በዋናነት በልጆች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርና በብዛት እድሚያቸዉ ከ5 ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የሚከሰትና ከ200 ኢንፌክሽኖች ውስጥ በአንዱ ላይ የማይቀለበስ ሽባነትን የሚያስከትል መሆኑ በስልጠናዉ የተገለፀ ሲሆን በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን በነሃሴ ወር 2012 ዓ.ም ሪፖርት የተደረገ መሆኑንና በኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ ዞን እና በደሴ ከተማ ለሚገኙ በጠቅላላዉ ከ8 መቶ ሃምሳ ሽህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡ በመድረኩም የፖሊዮ ዘመቻዉ በሚካሄድበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ሳይዘነጉ መሆን እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡
ዉጤታማ አፈፃፀሞችን በማስመዝገብ ሞዴል ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ተገለፀ፤

ዉጤታማ አፈፃፀሞችን በማስመዝገብ ሞዴል ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ተገለፀ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ጥቅምት 21/2013 ዓ.ም በደብረታቦር ከተማ አካሄደ፡፡ የዚህ ግምገማ ዓላማ በሩብ አመቱ ታቅደዉ የተከናወኑ፣ ያልተፈፀሙና በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባ ተግባራትን ለማመላከት ሲሆን በመድረኩ መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ኃይሌ እንደተናገሩት ባለፈዉ በጀት ዓመት ከኮቪድ-19 ክስተት ጋር በተገናኘ እንደ ተቋም የአንዳንድ ተግባራት አፈፃፀም ዝቅተኛ የነበሩ መሆኑን አዉስተዉ በያዝነዉ በጀት ዓመት የ10 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ትግበራ የጀመርንበት ወቅት በመሆኑና ይህንንም ታሳቢ ያደረገ ጉዞ የምንጓዝበት በመሆኑ በርካታ ስራዎች ከፊታችን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ዶክተር ማህተመ አያይዘዉም ከዚህ በኋላ የሚኖሩ ቀሪ የስራ ጊዜያት ዉጤታማ ተግባራትን ፈፅመን ሞዴል ተቋምና የማይበገሩ ባለሙያዎች ሆነን ወደ ኋላ የቀረዉን ወደፊት በማራመድ ለመጓዝ የምንቀጥልበትን መንገድ ለመነጋገርና፣ ስራዎችን አፋጥነን ለመቀጠል የምናደርግበት ነዉ ብለዋል፡፡ የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ በእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ በአቶ ለዓለም ገደፋዉ የቀረበ ሲሆን ባለፉት 3 ወራት በተቋሙ የነበሩ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች እንዲሁም መወሰድ ያለባቸዉ የመፍትሄ ሃሳቦች ተለይተዉ ቀርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በአሰራር ያጋጠሙና እንደ ክፍተት ከተነሱት ዉስጥ ምርምሮች በተያዘላቸዉ ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ብልሽትና በወቅቱ አለመጠገን፣ የግብዓት መቆራረጥ፣ ወርክሾፕ አለመኖር፣ የናሙና ዉጤት ቶሎ አለመድረስ፣ ከጤና ተቋማት ጋር የሚያስተሳስር የመረጃ ስርዓትና ዳታቤዝ አለመኖር፣ አጎበር አጠቃቀም ላይ ክትትል አለመኖር የመሳሰሉት ቀርበዋል፡፡ በዉይይቱ ማጠቃለያ ላይ ዶክተር ማህተመ እንዳሉት በመድረኩ የተነሱት ጥያቄና አስተያየት ጥሩ መሆናቸዉን ገልፀዉ ከነዉስን ችግሮችም ቢሆን ተቋሙ በጥሩ አቋምና አፈፃፀም ላይ መሆኑንና ይህም ዉጤት እስከታች ባለዉ የጤና መዋቅር የጋራ ርብርብ የተገኘ መሆኑን ገልፀዉ ተቋሙ ያገኘዉን ዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ ጥራት ማረጋገጫ ሙሉ እዉቅና ለማስቀጠል፣ በክልሉ የሚከሰቱ ወረርሽኝኞችን የመከላከል ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠልና ሌሎች ተግባራትን አቀናጅቶ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚጋጥሙ የግብዓት ችግሮችን ለመቅፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ፤

የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚጋጥሙ የግብዓት ችግሮችን ለመቅፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ፤

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚጋጥሙ የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ ሃይሌ እንዳሉት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያሉብን ችግሮች ላይ በመወያየት የመፍትሄ ሃሳቦችን በማስቀመጥ ወደፊት የተሻለ ስራ ለመስራት የሚጠቅም መሆኑን ገልጸው ሪፖርት እና የተሟላ መረጃ በወቅቱ በመስጠት ለህዝብ ተቆርቋሪነታችሁን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የመድረኩ ዓላማ ቀጣይ ወራት የወባ መስፋፊያ ወቅት በመሆኑ ያለብንን የግብዓት አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ወደፊት በምን ዓይነት መልኩ መስራት እንዳለብን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው፡፡ በመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን የተለያዩ ሃሶች ተነስተው ውይይት ተደርጓል፡፡ ከአብክመ ጤና ቢሮ፣ የኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ /የባህር ዳር፣ የደሴ እና የጎንደር ቅርንጫፍ ሃላፊዎች/፣ ከሁሉም ዞን ጤና መምሪያ የወባ ኦፊሰሮች እና አጋር አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡ “ወባን ማጥፋት ከኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 10-27/2013 ዓ.ም የወባ በሽታ መከላከልያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ለህብረተሰቡ በማስረፅ እና በመተግበር በክልል ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡
በክልላችን የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ ተጀመረ፤

በክልላችን የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ ተጀመረ፤

የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር ከጥቅምት 10-27/2013 ዓ.ም የሚከበረውን የወባ ሳምንት አስመልክቶ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ “ወባን ማጥፋት ከኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ቃል በክልል ደረጃ የሚከበረውን የወባ ሳምንት የወባ በሽታ መከላከልያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ለህብረተሰቡ በማስረፅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ የዘመቻው ዓላማ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ ሃይሌ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ላይ እንደተናገሩት በክልላችን ያለው የወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ የመጣ መሆኑን ገልፀልው የወባ ሳምንት መከበሩ የክልላችን ማህበረሰብ በወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ላይ አስፈላጊውን የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣና እንዲተገብር ያደርጋል ብለዋል፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ እንዳሉት የወባ በሽታ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ ተላላፊ በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን እና ይህን ለመከላከልና ለመቆጣጣር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልፀው የወባ ሳምንት ሲከበር የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር፣ የመኝታ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የወባ ምርመራ ማድረግ ለማህረሰቡ ግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መሰራት እንዳበት አሳስበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ፕሮግራም ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወ/ሮ ማስተዋል ወርቁ እንደገለፁት በያዝነው በጀት ዓመት በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል በ44 ወረዳዎች 217 ሺህ 393 ኪሎ ግራም የፀረ- ወባ ኬሚካል ተሰራጭቶ 340 ሺህ 39 ቤቶች የተረጩ መሆኑንና ከ988 ሺህ 881 ሰዎችን መታደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ በቆላማ እና በኢንቨስትመንት ያለባቸው ቦታዎች ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያ በማቋቋም ባለሙያዎችን ማሰማራት፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ ማሰማራት፣ ለማህረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ መስራት፤ የወባ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ማጠናከር እና የመኝታ አጎበር ማሰራጨት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሲሆን የፀረ ወባ ኬሚካልና መሳሪያ እጥረት መኖር፣ የወባ መድሀኒት አቅርቦት መቆራረጥ፣ አጎበርን በወቅቱ አለመተካትና አጎበርን የሚሸጡ ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ካጋጠሙ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ወ/ሮ ማስተዋል አስረድተዋል፡፡ የአማራ ክልል መሬት 80 በመቶው ለወባ መራቢያ ምቹ ሲሆን 68 በመቶው ህዝብ ደግሞ ለወባ ተጋላጭ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራትም 127 ሺህ 593 ሰዎች ተይዘዋል ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በቀጣይ የወባ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች የወባ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን ማጠናከር፣ በአጎበር አጠቃቀም ላይ ክትትል በማድረግ እና የማህበረሰቡን ግንዛቤ በመጨመር ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተላልፏል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው የትምህርትና የጤና መዋቅር የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተገለፀ

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው የትምህርትና የጤና መዋቅር የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተገለፀ

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው የትምህርትና የጤና መዋቅር የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተገለፀ፤
የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአብክመ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራት እና የወደፊት ስራዎች ላይ በባህር ዳር ከተማ መስከረም 26/2013 ዓ.ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ በመድረኩ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራት እና ትምህርት ቤቶች መልሰው ሲከፈቱ የሚሰሩ ስራዎች ምን መሆን አለባቸው የሚሉ ፅሁፎች ቀርበው፤ ከተሳታፊዎች በተነሱ አስተያየቶች እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የአብክመ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት እየቀነሰ የመጣውን የክልሉ የኮሮና የመመርመር አቅም መስተካከል እንዳለበት ገልፀው ወደፊት ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው የትምህርትና የጤና መዋቅር የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በመወጣት አገራዊ አደራውን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ሃይሌ በበኩላቸው በቅንነትና በቁርጠኝነት በርካታ ስራዎችን ሰርታችሁ እዚህ ደረጃ ላደረሱት የጤና ባለሙያዎች ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸው አሁንም ራሳችሁን ምሳሌ በማድረግ ህብረተሰቡን ማስተማር እና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ የክልሉ የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር የጤና ቢሮ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የዞን ጤና መምሪያ ሃላፊዎች፣ የዞን የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪዎች፣ የኮሮና የምርመራ ማዕከላት አስተባባሪዎች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡